ባለ ሦስት እግር ታክሲዎች ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡን አይደለም—-የደሴ ከተማ ነዋሪዎች

185

ደሴ መጋቢት 2 / 2011 በደሴ ከተማ ባለ ሦስት እግር ታክሲዎች በተመደቡበት የውስጥ ለውስጥ መስመር ባለመስራታቸው ሥራችንን በአግባቡ ማከናወን አልቻልንም ሲሉ ተገልጋዮች ገለጹ።

በተሰጣቸው የስምሪት መሰረት ለሕብረተሰቡ አገልግሎት በማይሰጡ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የከተማው መንገድ ትራንስፖርት መምሪያ አስታውቋል፡፡

በሆጤ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 06 ነዋሪ አቶ ሰይድ መሃመድ ለኢዜአ እንደገለጹት ታክሲዎቹ በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ባለመስራታቸው በየእለቱ ሩቅ መንገድ በእግር ተጉዘው ሥራቸውን ለማከናወን እየተሳናቸው ነው።

” አልፎ አልፎ በውስጥ ለውስጥ መስመር ቢሰሩም የሚያስከፍሉን የኮንትራት ሒሳብ ነው” ያሉት አቶ ሰይድ፣ ሦስት ብር ለሚያስከፍለው ከአሬራ-ወሎ ባህል አምባ አዳራሽ እስከ 20 ብር እየተጠየቁ መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ይመር ከድር”ከሽዋ በር መስጅድ-ሚካኤልና ከሽዋ በር-መንገሻ ጎራ የተመደቡ ባጃጆች በስምሪታቸው መሰረት ባለመስራታቸው በኮንትራት አንዳንዴም በእግር በመጓዝ ስራዬን ለማከናወን ተገድጂያለሁ” ብለዋል።

ባጃጆቹ ለሦስት ብር ታሪፍ  ከ15 ብር በላይ እያስከፈሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከባለ ሦስት እግር ታክሲ አሽከርካሪዎች መካከል ወጣት ሀሚድ ሸምሱ በተመደበበት ከወሎ ባህል አምባ-እንቁጣጣሽ  መስመር ተሳፋሪ አለመኖር ከቤንዚን እጥረት ጋር ተዳምሮ አገልግሎት ለመስጠት አዋጭ አመሆኑን ተናግሯል ።

“የምናገኘው ገቢ ከወጭያችን ጋር ስለማይመጣጠን ከታሪፍ በላይ ለማስከፈል አሊያም በኮንትራት ለመስራት ተገደናል” ብሏል ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ጌታነህ በበኩላቸው በተሰጣቸው ስምሪት መሰረት አገልግሎት በማይሰጡ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ወራት ከታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉና ከስምሪት ውጭ በኮንትራት ብቻ ሲሰሩ የተገኙ 84 የታክሲ አሽከርካሪዎች በገንዘብ መቀጣታቸውን  ለአብነት ጠቅሰዋል ።

“ትኩረት የሚሹ ቦታዎች ተለይተው ከባለድርሻ አካላት ጋር ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ በመሆኑ ችግሩ እየቀነሰ ነው” ብለዋል ።

“ተከስቶ የነበረው የከተማው የቤንዚን እጥረትም እየተቃለለ ነው” ያሉት ኃላፊው ሰበብ በመደርደር ከህግ ውጭ መስራት አግባብ ባለመሆኑ ህብረተሰቡም ድርጊቱን በመከላከል እንዲተባበር ጠይቀዋል ።

በደሴ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ከ900 በላይ ባለሶስት እግር ታክሲዎች መኖራቸው ታውቋል።