አምባሳደር መለስ ዓለም የሹመት ደብዳቤያቸውን አቀረቡ

97

አዲስ አበባ  መጋቢት 2/2011 በኬንያ የኤፌዴሪ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም የሹመት ደብዳቤያቸውን ለኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል የፕሮቶኮል ሹም ፒተር ሙዌንዴዎ አቀረቡ።

አምባሳደሩ ዛሬ ጠዋት ከምክትል የፕሮቶኮል ሹም ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

አምባሳደሩ በኬንያ አምባሳደር ሆነው በመሾማቸው መደሰታቸውን በመግለጽ የሁለቱን አገሮች ታሪካዊ እና ዘርፈ-ብዙ ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የሁለቱ አገሮች መሪዎች በአዲስ አበባና በናይሮቢ በቅርቡ ያደረጉት ጉብኝት እና በሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት የወዳጅነታቸው ማሣያ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ስራቸውም አጋዥ እንደሆነም አምባሳደር መለስ ጠቅሰዋል።

ምክትል የፕሮቶኮል ሹሙም ፒተር ሙዌንዴዎ በበኩላቸው አምባሳደር መለስ በቆይታቸው የኬንያ መንግስት ድጋፍ እንደማይለያቸው ተናግረዋል።

አምባሳደር መለስ በመጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በደረሰው የአውሮፕላን መከስከስ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች ቤተዘመዶች ከፍተኛ መጽናናትን ተመኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካውያን ኩራት ሆኖ እንደሚቀጥል እምነታቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም