ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

136
አዲስ አበባ ግንቦት 22/2010 ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የደቡብ ሱዳኑን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲትን ዛሬ በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። ሁለቱ መሪዎች በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዚሁ ጊዜ "የሁለቱ አገራት ግንኙነት በጠንካራ ወዳጅነት ላይ የተመሰረተ ነው" ብለዋል። ከፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ጋርም በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገልፀዋል። በኢትዮጵያ ሊቀመንበርነት የሚመራው ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ለተፈጠረው ግጭት መፍትሄ ለመስጠት በግጭቱ ውስጥ ተዋናይ የሆኑ ወገኖችን ሲያደራድር መቆየቱን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት አበክራ እንደምትሰራም ገልፀዋል። "በጎረቤት አገራት ሰላም ከሌለ በአገራችንም ሰላም ይኖራል ብለን አንጠብቅም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በጎረቤት አገራት ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ኢትዮጵያ የተለመችውን የልማትና የእድገት ውጥን ለማሳካት ሚና ያለው በመሆኑ ከጎረቤት አገራት ጋር በትብብር ትሰራለችም ብለዋል። የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት በበኩላቸው "ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ደጋፊ ጎረቤት ብቻ ሳትሆን አገራችንም ጭምር ነች" ብለዋል። ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን እንድታገኝ ላበረከቱት አስተዋፆም ምስጋና ችረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም