የተመድ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ባንዲራው ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ አደረገ

99

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2011 የተባበሩት መንግስታት ድርጀት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢ.ሲ.ኤ) በኢትዮጵያ አየር መንገድ በደረሰው አደጋ ህይወታቸው ባለፈው 157 ሰዎች  ሀዘን ባንዲራ ዝቅ ብሎ አንዲውለበለብ አደረገ።

መቀመጫው አዲስ አበባ የሆነው ኮሚሽኑ  የመንግስታቱ ድርጅት የተለያዩ ኤጀንሲዎች ኃላፊዎችና መላው ሰራተኛ በተገኙበት ዛሬ በተከናወነ ዝግጅት የሀዘን  መግለጫ ተላልፏል፤ ባንዲራ ዝቅ የማድረግ ስነ-ስርዓትም ተከናውኗል። 

የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉትሬዝ በአደጋው ለሞቱት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልፀዋል።

በአደጋው ከሞቱት 157 ሰዎች መካከል 17ቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አዘጋጅነት በኬንያ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ በሚካሄደው የአካባቢ ጥበቃ ስብስባ ለመሳተፍ ወደ ስፍራው እያቀኑ የነበሩ የድርጅቱ ሰራተኞች ናቸው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደህንነት ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ሆነው የአደጋውን መንስኤ ለማወቅ በሚደረገው እንቅስቃሴ በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲም በአደጋው የተሰማውን ሀዘን በመግለፅ ባንዲራም ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረጉን ባወጣው መረጃ አመልክቷል።

ወቅቱ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አብረን ቆመን ሀዘናቸውን የምንጋራበት ወቅት ነው ያለው  ኤምባሲው  ለኢትዮጵያ አየር መንገድና መንግሰት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

ከሟቾች መካከል ስምንት አሜሪካዊያን እንዳሉበትም ተመልክቷል።

ከአዲስ አበባ ናይሮቢ ኬኒያ ሲጓዝ የተከሰከሰው የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የ35 አገራት 149 መንገደኞችና ስምንት የበረራ አስተናጋጆችን ይዞ ነበር።

ከተሳፋሪዎቹ መካከል 32ቱ ኬኒያዊያን ሲሆኑ፤ 17ቱ ኢትዮጵያዊያን ቀሪዎቹ ደግሞ የሌሎች አገራት ዜጎች ናቸው።

አደጋው የደረሰበት ትናንት ማለዳ ከቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በተነሳ በስድስት ደቂቃ ልዩነት ነው። የአደጋው መንስኤ እስካሁን አልታወቀም።

የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅትንና ቦይነግን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ያሉት ኮሚቴ የአደጋውን መንስኤ በዚህ ሳምንት መመርመር እንደሚጀምርም የአየር መንገዱ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት በጋሻው ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም