በነጌሌ ቦረና ከተማ ጎዳና ተዳዳሪዎችን አምራች ለማድረግ የገንዘብና የመስሪያ ቦታ ድጋፍ ተደረገ

113

ነጌሌ መጋቢት 2/2011 ጎዳና ተዳዳሪ ወጣቶችን አምራች ለማድረግ ግማሽ ሚሊዮን ብርና የመስሪያ ቦታ ድጋፍ ማድረጉን የነጌሌ ከተማ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ታምሩ ታዬ ለጎዳና ተዳዳሪዎቹ የተሰጠው ሥልጠና ሲጠናቀቅ እንዳሉት ጽህፈት ቤቱ በመንግሥትና በተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ አዲስ ሕይወት ለሚጀምሩ 29 የጎዳና ተዳዳሪ ወጣቶች ድጋፍ አድርጓል።

በፈቃዳቸው ከጎዳና ህይወት ወጥተው ሥልጠና ከወሰዱት ወጣቶች መካከል ለ22ቱ 500 ሺህ ብርና 378 ካሬ ሜትር ቦታ መሰጠቱንም አስታውቀዋል፡፡

ወላጆቻቸውን በመቀላቀል በተረጋጋ ሕይወት መማር ለፈለጉ ሰባት ወጣቶች መቋቋሚያ 21 ሺህ ብር መበርከቱንም አቶ ታምሩ ተናግረዋል፡፡

ለወጣቶቹ በሥነ ምግባር፣ በአእምሮአዊ ግንባታና ዝግጅት፣ በማህበራዊ ሕይወትና በንግድ ሥራ ሙያ ላይ ያተኮረ የአንድ ወር ስልጠና መሰጠቱንም ገልጸዋል፡፡

የነገሌ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ከመከላከያ ሠራዊትና ከበጎ ፈቃደኛ ነዋሪዎችና ባለሀብቶች ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

የነጌሌ ከተማ ከንቲባ አቶ ባሊ በዱ በጎዳና ተዳዳሪ ወጣቶች ላይ የሚደርሰውን የሥነ ልቡና ጫና ለመቀነስ ድጋፍ ላደረጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ወጣቶች በጊዜያዊ ስሜት ተነሳስተው ራሳቸውን ከማህበራዊ ሕይወት በማግለል በአልባሌ ቦታ ጊዜያቸውን ከማባከን እንዲቆጠቡ መክረዋል።

ከወላጆቻቸው ጋር በፈጠሩት አለመግባባት ለሦስት ዓመታት የጎዳና ህይወት ያሳለፉት ጫልቱ ደስታና ቦሩ ደርሶ የጎዳና ሕይወት ተስፋ አስቆራጭና ለሥነ ምግባር ብልሹነት ስለሚዳርግ ሌሎች ከነዚህ በመማር ነገሮችን በትዕግሥት እንዲያሳልፉ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም