የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉትሬዝ በአውሮፕላን አደጋው የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለጹ

159

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2011 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉትሬዝ በኢትዮጵያ በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ለሞቱ ሰዎች የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገለጹ።

ትናንት ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን በቢሸፍቱና ሞጆ አካባቢ ኤጄሪ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ መከስከሱ ይታወቃል።

የበረራ ቁጥሩ ኢቲ 302 የሆነው ይህ አውሮፕላን 149 መንገደኞችንና 8 የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ በረራ ከጀመረ ከስድስት ደቂቃ በኋላ በመከስከሱ በውስጡ የነበሩ 157 ሰዎች ህይወት አልፏል።

ከሞቱት 157 ሰዎች መካከል 17ቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አዘጋጅነት በኬንያ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ በሚካሄደው የአካባቢ ጥበቃ ስብስባ ለመሳተፍ ወደ ስፍራው እያቀኑ የነበሩ የድርጅቱ ሰራተኞች ናቸው።

የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉትዬሬዝ "በአደጋው ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማቸው" መግለጻቸውን የአሜሪካው የዜና ወኪል አሶስዬትድ ፕሬስ በድረ ገጹ አስፍሯል።

ዋና ጸሐፊው በአደጋው ህይወታቸውን ላጡት ቤተሰቦችና ዘመዶቻቸው በተለይም ለኢትዮጵያ መንግስት ከልብ የመነጨ መጽናናትን የተመኙ ሲሆን ተመድ በአደጋው ከተጎዱ ወገኖች ጎን እንደሆነም አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች የምክር ቤትም ዛሬ ብሄራዊ የሐዘን ቀን እንዲሆን ወስኗል።

በመሆኑም የአገሪቷ ሰንደቅ አላማ ዛሬ (መጋቢት 2 ቀን 2011 ዓ.ም) በመላ ኢትዮጵያ ዝቅ ብሎ የሚውለበለብ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም