አባቶች በአድዋ ድል ያሳዩትን ቁርጠኝነት አዲሱ ትውልድ ተቀብሎ ለሰላምና ለዕድገት መሥራት አለበት -የአድዋ ተጓዦች

68

ድሬዳዋ መጋቢት 1/2011 አባቶች ለአገር ነጻነትና ሉአላዊነት መከበር በአድዋ ድል ያሳዩትን ቁርጠኝነት አዲሱ ትውልድ ተቀብሎ  ለሰላምና ለዕድገት መሥራት እንዳለበት የስድስተኛው የጉዞ አድዋ ተሳታፊዎች ጠየቁ።

የአድዋ ድል 123ተኛውን በዓል ለመዘከር  ከሐረር ተነስተው ለተጓዙት 48 ወጣቶች ትናንት በድሬዳዋ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

ተጓዦቹ  በሰጡት አስተያየት አባቶቻችንን ለድሉ መገኘት ያሳዩትን ቁርጠኝነት ይኸኛው ትውልድ ለአገሪቱ ሰላምና ዕድገት ማዋል ይገባዋል፡፡

በዚህም  አገሪቱን ወደ ታላቅነት ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ወጣት ሙሉጌታ ከበደ ጉዞው የአባቶችን ፅናትና ቁርጠኝነትን ምሳሌነት ለመከተል የተደረገ ጥረት ነው ብሏል፡፡

''በጉዟችን ላይ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኑነት የተጠናከረበት፤ ባህልና ልምድ የተለዋወጥንበት በመሆኑ አስደሳች ነው'' ሲልም ተናግሯል።

ወጣቶች የአባቶችን ወኔና ፅናት አንግበንና አንድነታችንን ጠብቀን ኢትዮጵያን ወደ ታላቅነቷ መመለስ ይገባናል በማለትም ወጣት ሙሉጌታ  ተናግሯል፡፡

ወጣት ዮናስ ተፈራ በበኩሉ እያበበ የመጣው ጉዞው ለአገር ሰላምና አንድነት መጠናከር አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ወጣት ትዕግስት አሸናፊ እቴጌ ጣይቱ በሴትነታቸው በአድዋ ድል ያሳዩትን ብልሃት ፣ጥበብና ቁርጠኝነት በመዋስ እሷም በጉዞው ተካፍያለሁ ትላለች፡፡

በመሆኑም ሴቶች የእቴጌ ጣይቱን ፈለግ በመከተል ለአገር ሰላም፣ ዕድገትና ለውጥ በመስራት ኢትዮጵያን ወደ ታላቅ ከፍታ ማድረስ ያሻል ስትልም አስተያየቷን ሰጥታለች።

''በአመራር ደረጃ ያሉትም ሆኑ እኛ ዜጎች ከመንደር አስተሳሰብ በመውጣት ለሁላችንን የምትበጅ አገር በአንድነት መገንባት ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን'' ብላለች፡፡

ወጣት በኃይሉ ሙሉጌታ የትግራይ እናቶች በጉዞው ወቅት ያደረጉላቸው አቀባበል እጅጉን አስደሳች እንደነበር መስክሯል፡፡

የተሻለችና የበለፀገች አገር ለመገንባት በሥርዓትና ሥነ-ምግባርን አጥብቆ መያዝ እንዳለበት አመልክቶ፣በዚህም ቤተሰብ ፣ ማህበረሰብና አገር በጠንካራ ሥርዓት ማደራጀት ወሳኝ መሆኑን ገልጿል፡፡

''ከቀድሞ አባቶቻችን የምማረው በዚህ ምግባር ራሳቸውን አንፀውና አንድነታቸው ጠብቀው የፈለጉትን ድል ማሳካት መቻላቸውን ነው'' ብሏል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል አፈ-ጉባዔ አቶ ከድር ጁሃር ወጣቶቹ የአያቶቻችንን ጀግንነት ለመዘከር ለ62 ቀናት ያደረጉት ጉዞና ድሉን የዘከሩበት መንገድ በአርአያነት እንደሚወደስ ገልጸዋል፡፡   

ወጣቶች በብሔር፣ በኀይማኖትና በሌሎች ጉዳዮች ሳይከፋፈሉ የተሻለችና የበለፀገች ሀገር ለመገንባት ሌት ተቀን መትጋት ይገባችኋል ሲሉም ምክራቸውን ለግሠዋል፡፡

''ድሬዳዋ በሰፈር እንጂ፤ በብሔር አትገለጽም'' ያሉት ምከትል አፈ ጉባዔው፣የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በፍቅርና በአንድነት የሚኖሩባት ከተማ መገለጫ እንደሆነች አስታውሰዋል፡፡

የድሬዳዋን እሴቶች ለጊዜያዊ ሥልጣንና ጥቅም ማዋልንና ሕዝብን ማፈናቀልን በማስቆም ለውጡን እንዲያስቀጥሉ አሳስበዋል።

ተጓዦቹን የድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮችና ነዋሪዎች አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን፣ የራት ግብዣም ተደርጎላቸዋል።

የከተማው ታዋቂ ገጣሚዎችና ከያንያንን የአድዋ ድልንና ተጓዦቹን የሚያሞገስ ሥራ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም