በአውሮፕላን መከስከስ በደረሰው አደጋ ጥልቅ ኀዘን እንደተሰማቸው ክልሎችና የድሬዳዋ አስተዳደር ገለጹ

66

መቀሌ/ሐረር/ድሬዳዋ/ባህርዳር/ጅግጅጋ መጋቢት 1/2011 በኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች በተከሰከሰው አውሮፕላ በደረሰው አደጋ ጥልቅ ኀዘን እንደተሰማቸው አራት ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታትና የድሬዳዋ አስተዳደር ገለጹ።

የትግራይ፣የሐረሪ፣የአማራ፣የሶማሌና ደቡብ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች መንግሥታትና አስተዳደሩ ባወጡት መግለጫ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር በተከሰከሰው አውሮፕላን በ157 ሰዎች ላይ በደረሰው ሞት እንዳዘኑ አስታውቀዋል።

አደጋው መላውን የክልሎቹን ሕዝብ ያሳዘነና እጅግ ከባድ መሆኑን ገልጸው ፣የሟቾቹን  ነፍስ ፈጣሪ በገነት እንዲያኖርም ተመኝተዋል።

የአደጋው ሰለባ ለሆኑ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎች ቤተሰቦች ፣ ወዳጆችና ለኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትም እንደሚመኙ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የላኩት መግለጫ ያስረዳል።

ስሪቱ የቦይንግ ኩባንያ የሆነው 737 አውሮፕላን ለስድስት ደቂቃ ብቻ በአየር ላይ ከቆየ በኋላ የተከሰከሰው በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ጊምቢቹ ወረዳ ውስጥ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኑን ከኩባንያው ከተረከበው የአራት ወራት ዕድሜ እንዳለው ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረማርያም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ከጠዋቱ 2ሰዓት ከ44  ደቂቃ ላይ በደረሰው አደጋ  የ33 አገር ዜግነት ያላቸው መንገደኞችና የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ሕይወት አልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም