የአፈር ጤንነትና ለምነት ማሻሻያ ስትራቴጂ ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ሊደረግ ነው

52
አዳማ ግንቦት 22/2010 በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ የአፈር ጤንነትና ለምነት ማሻሻያ ስትራቴጂ ሰነድ ማዘጋጀቱን የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ስትራቴጂውን ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ መክሯል። በዚህ ወቅት የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በአፈር ጤናማነትና ለምነት በኩል ካሉ ማነቆዎች መካከል የተፈጥሮ ማዳበሪያን በተገቢው ሁኔታና መጠን በስፋት ጥቅም ላይ አለማዋል ይጠቀሰል። በተለይ በአፈር መጎሳቆልና ብክለት ምክንያት የአፈር ምርታማነት መቀነስና ጤናማነት መታወክ እንዲሁም ዘርፉ ወጥ የሆነ ስትራቴጂ  የሌለው መሆኑ ተጨማሪ እንቅፋት መሆኑን ነው የተናገሩት። በመሆኑም ለአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው ስትራቴጂ ሰነድ በአፈር ጤናማነትና ለምነት ላይ የሚስተዋሉ አብይ ማነቆዎችን ከመለየት ባለፈ መፍትሄዎችን በዝርዝር ማስቀመጡን አስታውቀዋል። ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉልና አማራ ክልሎችን ጨምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነውን አሲዳማ አፈር ለማካም የኖራ አቅርቦቱን ለማቀላጠፍ ስትራቴጂው ወሳኝ መሆኑንም አስረድትዋል። እንደዶክተር ካባ ገለጻ ስትራቴጂው በከፍተኛ ደረጃ የተጎዳው የተፈጥሮ ሀብት እንዲያገግምና በዘላቂነት እንዲጠበቅ የሚያደርግ ከመሆኑ በተጨማሪ የመንግስትን የረጅም ጊዜ የልማት ዕቅድ ታሳቢ ያደረገ ነው። ከእዚህ በተጨማሪ ስትራቴጂው በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ሊፈቱ የሚገባቸውን የአፈር ጤንነትና ለምነት ማነቆዎችንና የመፍትሄ ሀሳቦችን በዝርዝር መያዙን ነው የገለጹት። ስትራቴጂው ለቀጣዮቹ 10 ዓመታት የሚተገበረው በዋናነት በአነስትኛ ማሳ ላይ መሆኑን ገልጸው ይህም አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮችን ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግና አገራዊ ዕድገቱን ለማፋጠን ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል። በግብርናና እንስሳት ሃብት  ሚኒስቴር የአፈር ለምነት ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ሰለሞን በበኩላቸው በስትራቴጂው ሰነድ ዝግጅት ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የፌዴራልና የክልል የግብርና ምርምር ተቋማት እንዲሁም በአፈር ለምነት ዙሪያ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ተሳትፈዋል። ስትራቴጂው ወደ ክልሎች ወርዶ በ2011 የዕቅዳቸው አካል አድርገው ተግባራዊ በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ታስቦ አውደ ጥናቱ መዘጋጀቱንም አመልክተዋል። ከስትራቴጂው ዝግጅት ተሳታፊዎች መካከል የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ የአፈር ሳይንስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዋሴ ኃይሌ በሰጡት አስተያየት በአገሪቱ የሰብል ምርታማነትን እንዲቀነስ ከሚያደርጉ ዋናው ቁልፍ ነገሮች መካከል የደን መጨፍጨፍ፣ መሬትን በተደጋጋሚ ማረስና የአፈር ጤንነት መጓዳል መሆናቸውን ተናግረዋል። እነዚህን ችግሮች ለመከላከልና የአፈር ሀብት አያያዝና አጠቃቀም ቅንጅታዊ አሰራርን በማስፈን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ስትራቴጂው ወሳኝ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁሉም አካላት የድርሻውን እንዲወጣ አመልክተዋል። ለሁለት ቀናት በተዘጋጀውና ዛሬ በተጠናቀቀው በዚህ አውደ ጥናት ላይ ከክልል፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከልማት አጋሮች የመጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም