የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና ሕዝብ አውሮፕላኑ በደረሰበት ድንገተኛ አደጋ ኀዘኑን ገለጸ

757

ጋምቤላ  መጋቢት 1/2011 የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና ሕዝብ የኢትየጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በደረሰበት ድንገተኛ አደጋ  የተሰማውን ኀዘን ገለጸ።

ምክር ቤቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ በመጓዝ ላይ የነበረው አውሮፕላን በደረሰበት አደጋ በእጅጉ አዝኗል።

በአደጋው ሕይወታቸው ላለፉ ዜጎች ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን ተመኝቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እያበረከተ ካለው አስተዋፆ በተጨማሪ ኢትዮጵያን በዓለም እንድትታወቅ ያደረገ አገራዊ ተቋም መሆኑንም መግለጫው አስታውሷል።

በምሥራቅ ሸዋ ዞን ጊምቢቹ ወረዳ ቱሉ ፈራ በሚባል የገጠር ቀበሌ ክልል የወደቀው አውሮፕላን በአየር ላይ የቆየው ለስድስት ደቂቃ ብቻ ነበር።

አውሮፕላኑ 157 ተሳፋሪዎች የነበሩት ሲሆን፣ከነዚህም ስምንቱ የአየር መንገዱ ሠራተኞች ናቸው።