በጋምቤላ ክልል በተፈጥሮ ደን ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል አጥጋቢ ሥራ አልተሰራም – የምክር ቤት አባላት

633

ጋምቤላ የካቲት 1/2011በጋምቤላ ክልል በተፈጥሮ ደን ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል አጥጋቢ ሥራ አለመከናወኑን አንዳንድ የምክር ቤት አባላት  ገለጹ።

የክልሉ የአካባቢ  ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ የተፈጥሮ ደኑን ከጥፋት ለመታደግ የወጣው ረቂቅ ዓዋጅ የማስፈጸሚያ ደንብና መመሪያ ስላልተዘጋጀለት እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ተቸግሬያለሁ ይላል።

አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት እንደተናገሩት በክልሉ የተፈጥሮ ደን ላይ ጭፍጨፋና ቃጠሎ ጉዳት እየደረሰበት ነው።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ኡጉላ ኡጁሉ ለከሰል፣ ለግንባታ፣ ለማገዶና ሌሎች ፎጆታዎች ሲባል በክልሉ የደን ሀብት ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት እየደረሰበት መሆኑን አመልክተዋል።

የእርሻ መሬት ለማስፋፋት፣ አዲስ የግጦሽ ሳር ለማግኘትና ለሌሎችም ጉዳዮች  ሲባል በሚለኮስ የሰደድ እሳትም ጉዳቱን እያባባሰው መሆኑን ተናግረዋል።

የደን ሀብት አያየዝና አጠቃቀምን አስመልከቶ የወጣውን ረቂቅ ዓዋጅ ሥራ ላይ በማዋል ችግሩን መከላከል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የጋምቤላ ከተማ ምክር ቤት አባል  አቶ ዮኒያስ ተኮምሳ በበኩላቸው የደን ረቂቅ አዋጁን ተግባራዊ በማድረግ በተፈጥሮ ደን  ላይ ጉዳት በሚያደረሱ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ ጎን ለጎን በተፈጥሮ ደን ሀብት ላይ ጉዳት በሚያደረሱ  አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ ካልተወሰደ ችግሩን ማስቆም እንደማይቻል ጠቁመዋል።

የክልሉ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮኒያስ አበበ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በግብርና ኢንቨስትመንትና በኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማነስ  ምክንያቶች በክልሉ የተፈጥሮ ደን ሀብት ላይ ጉዳት ሲደርስ መቆየቱን ተናግረዋል።

ከግብርና ኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ የነበረው ችግር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቢቃለልም ፤በህብረተሰቡ የሚደረሱው ጉዳት አለመቀነሱን አስታውቀዋል።

የተፈጥሮ ደን ሀብቱን ለመከለካል ረቂቅ አዋጅ ቢወጣም የማስፈጸሚያ ደንብና መመሪያ ባለመዘጋጀቱ በደን ላይ ጉዳት በሚያደርሱ አካላት እርምጃ ለመውሰድ ችግር ሆኖባቸው መቆየቱን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት የአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብና መመሪያ እንዲዘጋጀለት ለሚለከተው አካል ማቅረቡንና የቢሮውን የአደረጃጀት እስከ ወረዳ በማዝለቅ ችግሩን ለመከላከል ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

በክልሉ ማጃንግ ዞን የሚገኘውንና  በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ የትምህርትና ባህል ማዕከል/ዩኔስኮ/ የተመዘገበውን የተፈጥሮ ደን ሀብት ጨምሮ ከክልሉ አጠቃለይ የቆዳ ስፋት   16 ከመቶ የሚሆነው በተፈጥሮ በደን የተሸፈነ ቢሆንም፤ በበጋው ወራት በሚከሰት የሰደድ እሳት ከ40 እስከ 60 ሺህ ሄክታር የሚደርስ የደንና የግጦሽ መሬት ቃጠሎ እንደሚደርስበት መረጃዎች ያመለከታሉ።