ተቋርጦ የነበረው የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ተጀመረ

79
አዲስ አበባ ግንቦት 22/2010 ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ዛሬ ተጀምሯል። ተደራዳሪ ፓርቲዎቹ ድርድሩ በ"ብሄራዊ መግባባት" ርእሰ ጉዳይ ዙሪያ ሊካሄድ በሚችልበት አቅጣጫና ሊኖረው በሚገባው ማእቀፍ ላይ የተወያዩ ቢሆንም በስምምነት መቋጨት ባለመቻላቸው በቀነ ቀጠሮ ተለያይተዋል። ፓርቲዎቹ የመላ አማራ ህዝብ ድርጅት/መአህድ/ ወደ ድርድሩ ለመመለስ ባለፈው ሚያዝያ ወር 2010 ባቀረበው ጥያቄ ላይ ከተወያዩ በኋላ ጥያቄውን ተቀብለው ፓርቲው የድርድሩ አካል እንዲሆን ወስነዋል። ፓርቲዎቹ ድርድሩ ላለፉት ወራት የተቋረጠበትን ምክንያት አጀንዳቸው አድርገው የተነጋገሩ ሲሆን በዚህ ዙሪያ የኢህአዴግ ተወካይ በሰጡት ማብራሪያ ድርድሩ የተቋረጠው ሌሎች አንገብጋቢ ሀገራዊ ጉዳዮች በማጋጠማቸው መሆኑን ገልፀዋል። በተለይም ባለፉት ወራት በህዝቡ የተነሱ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ መንግስት በተለያዩ እንቅስቃሴዎች መጠመዱ የድርድሩ ሂደት እንዲቋረጥ ምክንያት ሆኗል ሲሉም ተናግረዋል። ለውይይቱ ከተቀረፁት የተለያዩ የመወያያ አጀንዳዎች መካከል በአምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው "የብሄራዊ መግባባት" ጉዳይ  ከሁሉም አጀንዳዎች መቅደም የሚገባው ነበር ሲሉም ተደራዳሪ ፓርቲዎቹ ገልፀዋል። የብሄራዊ መግባባት ጉዳይ የፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን መላው የሀገሪቱ ህዝቦችን በቀጥታ የሚመለከት ጉዳይ በመሆኑ ከበፊቶቹ የመወያያ አጀንዳዎች በተለየ መንገድ ሊካሄድ እንደሚገባም ተሳታፊዎቹ አሳስበዋል። በዚህም መሰረት በብሄራዊ መግባባት ርእሰ ጉዳይ ዙሪያ የሚካሄደው ድርድር ሊይዝ በሚገባው አቅጣጫና ማእቀፉ ላይ ተደራዳሪ ፓርቲዎቹ መክረዋል። ያም ሆኖ ጉዳያቸውን በስምምነት መቋጨት አልቻሉም። ለዚህ ደግሞ ከተደራዳሪ ፓርቲዎቹ መካከል 12ቱ የድርድር ሂደቱንና ማዕቀፎቹን የሚያቀናጅ ኮሚቴ ሊኖር ይገባል የሚል ሀሳብ ሲያቀርቡ በሌላ በኩል ደግሞ መላው ኦሮሚያ ህዝብና የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲዎች በመተዳደርያ ደንቡ መሰረት በቀጥታ ወደ ድርድር መግባት አለብን በሚል በመከራከራቸው ነው። የኢህአዴግ  ተወካይ በበኩላቸው በብሄራዊ መግባባት ርእሰ ጉዳይ ላይ የሚካሄደው ውይይት "አቅጣጫ ምን መምሰል አለበት" በሚለው ዙሪያ ከተደራዳሪ ፓርቲዎች የቀረቡትን ሃሳቦች አቀናጅቶና አደራጅቶ ድርድሩን መቀጠል ይቻላል የሚል ሀሳብ አቅርቧል። "ፓርቲዎቹ በራሳችሁ መንገድ ኮሚቴ ማቋቋም ትችላላችሁ፤ ያም ሆኖ ኢህአዴግ  ግን አባል አይሆንም፤" ሲሉ ተወካዩ ገልፀዋል። በዚህም የተነሳ የድርድሩ ተሳታፊዎች ከስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻላቸው ውይይታቸውን በመጪው ሳምንት ማክሰኞ ለመቀጠል ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል። ተደራዳሪዎቹ በተከታዩ ስብሰባቸው የታሰበው ኮሚቴ ስልጣንና ኃላፊነት ምን መሆን አለበት በሚለው ጉዳይ በመወያየት ውሳኔ ያሳልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ኢህአዴግ በሚቋቋው ኮሚቴ ውስጥ አባል የመሆኑን ጉዳይ እንዲያስብበትም ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም