በሁለቱ ህዝቦች መካከል የሰላም ግንባታዋን እንደምታጠናክር የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ገለጸች

86

ዲላ መጋቢት 1/2011 በጌዴኦና ጉጂ ህዝቦች መካከል የጀመረችውን የሰላም ግንባታ ሥራ እንደምታጠናክር የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አስታወቀች ፡፡

በቤተክርስቲያኗ የሐዋሳ አገረ ስብከትና የካቶሊክ እርዳታ ድርጅት "ሲ አር ኤስ" በመተባበር በጌዴኦና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ለሚገኙ ምሁራንና የሃይማኖት መሪዎች የሥልጠናና የጋራ የምክክር መድረክ አዘጋጅተዋል፡፡

የአገረ ስብከቱ የማህበራዊና ልማት ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ማቴዎስ ዳንጊሶ እንደተናገሩት ቤተክርስቲያኗ በአካባቢው የጸጥታ ችግር ከተፈጠረበት ጊዜ አንስታ በሰላም ዙሪያ የተለያዩ ተግባራትን አከናውናለች፡፡

ረጂዎችን በማፈላለግ የነፍስ አድን ሰብዓዊ ማድረጓንና ከእርዳታ ድርጅቱ ጋር በመተባበር በመልሶ ማቋቋምና በሰላም ግንባታ ሂደት ላይ እገዛ እያደረገች መሆኑን አስረድተዋል።

እስካሁን በነበረው የሰላም ግንባታ ሥራ የጌዴኦና የምዕራብ ጉጂ ዞኖች አመራሮች፣ፖሊሶች፣ የሃይማኖትና የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ወጣቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅርበት ተወያይተው የጋራ መፍትሔ እንዲያበጁ ቤተክርስቲያኗ የአስተዋጽኦ ማበርከቷን አብራርተዋል።

በቤተክርስቲያኗ የተዘጋጁ መድረኮች በወጣቶች ዘንድ መልካም የሆነ መነቃቃት መፈጠሩን ገልጸው፣ በጋራ መድረኮች ላይ የተሳተፉ ወጣቶች ወደ የአካባቢያቸው ተመልሰው ተስፋ ሰጪ ሥራዎችን እየሰሩ ነው ብለዋል ፡፡

ሁለቱ ህዝቦች ወደቀደመ ወንድማማችነታቸው ተመልሰው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር እስኪፈጠር ድረስ ቤተክርስቲያኗ የጀመረችውን የሰላም ግንባታና ድጋፍ ሥራ እንደምታጠናክርም አመልክተዋል ፡፡

የሁለቱ ዞኖች ምሁራን ከብሔርተኝነት የጸዳ መፍትሔ አመላካች ጥናቶችን በማድረግ ሕዝቦቹን ማቀራረብ እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡

የሃይማኖት መሪዎችም አባታዊ ስብዕናን በመላበስ ሰላምና አንድነትን ለማምጣት መትጋት እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል ፡፡

በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተርና የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ገልቹ ጃርሶ የጌዴኦና ጉጂ ህዝቦችን አንድነት ለማጠናከርና በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በሚደረገው ጥረት ምሁራን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዳልተወጡ አብራርተዋል።

"ምሁር ማለት ከዘረኝነት አስተሳሰብ የተላቀቀ ማንነት ያለው ነው" ያሉት መምህር ገልቹ ፣በተለይ የቡሌ ሆራና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ሁለቱን ህዝቦች አንድ በሚያደርጓቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግና ከአድልኦ የጸዳ ጥናት በማካሄድ ወንድማማችነታቸውን ለማጠናከር መስራት አለብን ብለዋል ፡፡

ምሁራኑ የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱ መድረኩ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በዲላ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ትምህርት ክፍል የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት ዮሴፍ ማሩ በበኩላቸው ሁለቱም ህዝቦች የገዳ ሥርዓትን የሚከተሉና አንድ የሚያደርጓቸው ባህላዊ ክዋኔዎች ያሏቸው እንደሆኑ አመልክተዋል።

ለአብሮነታቸው መጠናከር መሰረት የሆኑ የጋራ እሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩና ለትውልድ የሚተላለፉ ጥናቶችን በማካሄድ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በምዕራብ ጉጂ ዞን ዲንቱ ሀምበላ ወረዳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያ ሊቀ ካህናት መምሬ አስማረ ጫኔ"የሃይማኖት መሪዎች ከወገንተኝነት ይልቅ የሁሉንም እምነት ተከታዮች በእኩል አይን በማየትና መንፈሳዊነትን ተላብሰን መስራት ይጠበቅብናል"ብለዋል ፡፡

የሁለቱ ዞኖች የሃይማኖት መሪዎች በጋራ መሥራት ከጀመሩ ወዲህ አበረታች ለውጦች እየታዩ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የጌዴኦ ዞን የሃይማኖት ጥምረት አባል የሆኑት አቶ ይርጋና አሽኔ በበኩላቸው "ራሳችንን አሳልፈን እስከመስጠት በቁርጠኝነት ከሰራን ሁለቱን ህዝቦች ወደቀድሞ አንድነታቸው መመለስና ዘላቂ ሰላም ማምጣት እንችላለን" ብለዋል ፡፡

ለአራት ቀናት በተካሄደው የሥልጠናና ምክክር መድረክ በሁለቱ ዞኖች በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግሥት  ኃላፊዎች ተገኝተዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም