በሰሜን ሸዋ ዞን ለመጀመሪያ ጊዜ ከ28 ሺህ ኩንታል በላይ ቡና ተመረተ

79

ፍቼ መጋቢት 1/2011 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ለመጀመሪያ ጊዜ ከ28 ሺህ ኩንታል በላይ የቡና ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

ምርቱ የተሰበሰበው ደራ ፣ሂደቡ አቦቴና ወረ-ጃርሶ ወረዳዎች ከለማው 455 ሄክታር መሬት ላይ መሆኑን በጽህፈት ቤቱ የቡና፣ፍራፍሬና  ቅመማ ቅመም ሥራ ሂደት  ባለቤት አቶ ሰለሞን  አሰፋ ገልጸዋል።

በልማቱም ከመደበኛ የሰብል ልማት ጎን ለጎን ከ10 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን አስታውቀዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት 800 ሄክታር መሬት ቡና እንክብካቤ እየተደረገለት መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም 136 ሞዴል አርሶ አደሮች የራሳቸውን የቡና ችግኝ ማዘጋጃ ጣቢያዎች በማቋቋም ለአካባቢው ተስማሚ ችግኞችን በማፍላት ከራሳቸው አልፈው ለአጎራባች ወረዳዎች  ለማፍላት እየሰሩ ነው ብለዋል።

በዞኑ የደራ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበበው ግርማ በበኩላቸው በወረዳው በቡና ልማት ኤክስቴንሽን ለተሳተፉ አርሶ አደሮች በየዓመቱ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ 200 ሺህ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች እየተሰራጩ  መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቡና ልማቱ በመሳተፍ ላይ ካሉት የደራ ወረዳ የባላ ቀበሌ አርሶ አደሮች መካከል ሙራድ ሁሴን ከቡና ምርቱ መጠነኛ ገቢ በቅርቡ ማግኘታቸውን ገልጸው፣ ለወደፊትም ልማቱን በማስፋፋት ገቢያቸውን ለማሳደግ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የግብርና ባለሙያዎች የሚሰጧቸውን ምክርና ድጋፍ ተግባራዊ በማድረግ በሄክታር 10 ኩንታል ለማምረት ጥረት እያደረጉ ነው።

ሌላው የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ግርማ ዋቅጅራ በሙከራ ደረጃ የጀመሩትን  የቡና ልማት በመጪው ክረምት ለማስፋፋት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም