የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የአንድ አባሉን ያለመከሰስ መብት አነሳ

86

አሶሳ የካቲት 30/2011 የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ በካማሽ ግጭት የተጠረጠረ አንድ የምክር ቤት አባልን ያለመከሰስ መብት በማንሳት ማምሻውን ተጠናቀቀ፡፡

ከትናንት ጀምሮ በአሶሳ ሲካሄድ በቆየው የክልሉ ምክር ቤት ስምንተኛ መደበኛ ጉባኤ የክልሉ መስተዳድር እና የክልል ምክር ቤት ጽህፈት ቤቶች፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት የ2011 የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ተመልክቷል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በሪፖርቶች ላይ በጥልቀት በመወያየት በቀጣይ ሊሻሻሉ ይገባል ባሏቸው ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

በጉባኤው አቶ አበራ ባዬታ እና አቶ ሙለታ ወምበር በፌዴሬሽን ምክር ቤት ያላቸውን የክልሉን ህዝብ ውክልና በማንሳት በምትካቸው የምክር ቤቱ ዋና አፈ-ጉባኤ እና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሆኑትን አቶ ሃብታሙ ታዬና አቶ አድጎ አምሳያን አስቀምጧል፡፡

የ17 የወረዳ እና የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች እና የዳኞች ሹመትም ጸድቋል፡፡

እንዲሁም የክልሉን የ2011 ተጨማሪ በጀት፣ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ረቂቅ ማሻሻያ አዋጆችም የምክር ቤቱ አባላት በስፋት ተወያይተው ያጸደቋቸው ናቸው፡፡

የምክር ቤቱ ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ሐብታሙ ታዬ እንዳስታወቁት ምክር ቤቱ የክልሉ ውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ የሆኑትን አቶ ጸጋዬ ተሠማን ያለመከሰስ መብት በአብላጫ ድምጽ አንስቷል።

ዋና አፈ-ጉባኤው እንደሚሉት የህግ ከለላው የተነሳው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ መስከረም ወር 2011 ዓ.ም. እና ከዚያ በፊት በክልሉ ካማሽ ዞን በተፈጠረ ግጭት በሞቱ በርካታ ሰዎች ወንጀል ስለመጠርጠራቸው ነው፡፡

ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለምክር ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ አቶ ጸጋዬ በግጭቱ ወቅት በዞኑ የሚገኙ ተሰናባች የመከላከያ ሠራዊት እና የሚሊሻ አባላትን “ጋሽላይ ” ወይም ወጣቶች በሚል ስያሜ በማደራጀት፣ በማሰልጠንና ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በማስታጠቅ ወንጀሉን ሲያስተባብሩ እንደነበር የሚያመላክት መረጃ እንዳለው መግለጹን ለምክር ቤቱ አስረድቷል፡፡

ስድስት የሚሆኑ የምክር ቤቱ አባላት የህግ ከለላውን መነሳት ባይቃወሙም በጠቅላይ አቃቤ ህግ ገለልተኛነት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው በዚሁ ወቅት ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አድጎ አምሳያ “በሀገሪቱም ሆነ በክልሉ መልኩን እየቀያየረ የተከሰተው ግጭት መንግስት ፈተና ውስጥ ከትቶ እንደነበር መርሳት የለብንም” ሲሉ ለምክር ቤቱ አባላት አስታውሰዋል፡፡

“የምክር ቤቱ አባላትም ሠላምን ለማስጠበቅ በወንጀል የተጠረጠሩ አባላትን አሳልፈው መስጠት ብቻ ሳይሆን እስከ ህይወት መስዋዕትነት መክፈል ይገባናል” ብለዋል፡፡

ሕጋዊ የሆነው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የወንጀል ማጣራት ሥራን ባልተጨበጠ መረጃ መከላከልም ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም