አፋን ኦሮሞ ተጨማሪ የፌዴራል የስራ ቋንቋ ቢሆን ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው---የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች

217

አምቦ የካቲት 30/2011 አፋን ኦሮሞ ተጨማሪ የፌዴራል የስራ ቋንቋ ቢሆን ህብረተሰቡ ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር እሴቶችን ለመለዋወጥ ይረዳል ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ አርቲስቶች ገለጹ።

“አፋን ኦሮሞ የፌዴራል የስራ ቋንቋ  ቢሆን ያለው ተቀሜታ” በሚል ዙሪያ  ለሁለት ቀናት ሲካሔድ የቆየው ሲምፖዚየም ተጠናቀቀ።

አስተያየታቸውን ከሰጡት አርቲስቶች መካከል አርቲስት አበበች አጀማ እንዳለችው አፋን ኦሮሞን የፌዴራል የስራ 

ቋንቋ ለማድረግ ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር መወያየት ያስፈልጋል፡፡

“የኦሮሞ ህዝብ ልጆቹ ቋንቋውን አውቀው ለሌሎች እንዲያሳውቁ ማድረግ ይኖርበታል” ያለችው አርቲስቷ ሌሎች ብሄረሰቦችም ይሄንኑ ጥረት በማገዝ ለቋንቋው እድገት እንዲሰሩ ጠይቃለች።

አርቲስት ፍቅሬ አምሳሉ በበኩሏ "ሀገሪቷ  በአንድ  የፌዴራል  ቋንቋ ብቻ መጠቀሟ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲተያይ ወደ ኋላ መቅረቷን ያሳያል ሲለዚህ አፋን ኦሮሞን በተጨማሪ የፌዴራል ቋንቋነት መጠቀሙ ያስፈልጋል" ብላለች።

ሌላው ተሳታፊ ጋዜጠኛና ደራሲ ኢሳያስ ሆርዶፋ "የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በቋንቋው  ጠቀሜታ ዙሪያ ጥናቶችን ሊያበረክቱ ጋዜጠኞችም ለቋንቋው እድገት የበኩላቸውን ድርሻ  ሊወጡ ይገባል" ብሏል።

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር  ገረመው ሁሉቃ አፋን ኦሮሞን የፌዴራል የስራ ቋንቋ ለማደረግ የቴክኒኪ ኮሚቴን የማዋቀር ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የክልሉ መንግስት ይህን ጉዳይ በተጠናከረ መልኩ እንዲሄድበት ቢሯቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገበተዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ትብብር  በተዘጋጀው በዚሁ በሲምፖዚየም ላይ የተለያዩ ምሁራን ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፥ ያንን መሰረት በማድረግ ውይይት ተካሄዶበታል፡፡

በዚሁ ሲምፖዚየም ላይ ከፌዴራል ከክልሎች  ከዞንና ከከተማ አስተዳደሮች  የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም