በምስራቅ ወለጋ ዞን ኦንኮ-ሰርክያሲስ በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል ለህብረተሰቡ መድኃኒት እየታደለ ነው

115

ነቀምት የካቲት 30/2011 በምስራቅ ወለጋ ዞን ኦንኮ-ሰርክያሲስ የተባለ የእከክ በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል ለህብረተሰቡ  መድኃኒት በዘመቻ እየታደለ መሆኑን  የዞኑ የጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ሰውነትን በከፍተኛ ደረጃ ከማሳከክ ባለፈ ለዓይነ ስውርነት የሚዳርገውን ይሄው በሽታ ለመከላከል ከትናንት ጀምሮ መድኃሀኒት በነጻ እየታደለ   መሆኑን በጽህፈት ቤቱ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሽፈራው ከበደ ገልጸዋል፡፡

በዘመቻ እየተካሄደ ባለው የመድኃኒት እደላው በዞኑ 17 ወረዳዎች የሚገኙ 286 ቀበሌዎች የሚኖሩ ከአንድ ሚሊዮን  በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል፡፡

እስከ መጋቢት 3/2011ዓ.ም  በሚቆየው በዚሁ ዘመቻ መድኃኒቱ የሚሰጠው ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በላይ ለሆኑ ታዳጊዎችና አዋቂዎች እንደሆኑ ያመለከቱት አስተባባሪው ለነፍሰ ጡር እናቶች  ግን እንደሚይሰጥ አስታውቀዋል።

የበሽታው ምልክት በዞኑና አጎራባች ክልሎች መታየቱን ቀደም ሲል በተካሄደው ጥናት መረጋገጡን ያመለከቱት አቶ ሽፈራው "የበሽታው እስኪገታ የመድኃኒት እደላው ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም