ፖሊስ በርካታ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችና የውጭ አገሮች የገንዘብ ኖት ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር አዋለ

62

አደስ አበባ የካቲት 30/2011 ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልገሎት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ባደረጉት ክትትል በርካታ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችና የውጭ አገሮች ገንዘብ ኖት ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር አዋለ።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች የተጠሩት የጎዳና ላይ የሠላማዊ ሰልፍ እንቅስቃሴዎች ምንም አይነት ፍቃድ አለመሰጠቱንም ኮሚሽኑ ስታውቋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ ዘላለም መንግሥቴ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በተሰራ ሥራ በርካታ ሕገ-ወጥ መሣሪያዎቹና የውጭ አገሮች የገንዘብ ኖቶቹ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

በዚህም 28 ክላሽንኮቭና 459 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ ተይዟል።

ያም ብቻ ሳይሆን ባለፉት ስድስት ቀናት በተደረገው ክትትል በአዲስ አበባ የሽብር ተግባራትንና ሌሎች እኩይ ተግባራትን ለመፈጸም የሚሰራ ቡድን አባላት መያዛቸውን ጠቁመዋል።

ምንም እንኳን ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውሩን ለመግታት በመንግሥትና በሚመለከታቸው አካላት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ ቢሆንም እንቅስቃሴው አሁንም አለመቆሙን ጠቁመዋል።

ይህንንም ከግምት በማስገባት ኅብረተሰቡ ከፖሊሰ ጎን በመቆም የመጠቆምና የማጋለጥ ሥራ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል በአዲስ በአበባ በማኅበራዊ ሚዲያ የተጠሩ የጎዳና ላይ የሠላማዊ ሰልፍ እንቅስቃሴዎች ምንም አይነት ፈቃድ አለመስጠቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

በመሆኑም ከዚህ አግባብ ውጪ በሚካሄዱ ሰልፎች አጋጣሚውን በመጠቀም የሽብርና ተግባራት ሊፈጽሙ የሚችሉ አካላት ስለሚኖሩ ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በመዲናዋ ያለ ፈቃድ ሠልፍ የሚያካሄዱ አካላትም ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸው ሠልፍ ለማድረግ ግን ህጋዊ አሰራሩን መከተል እንደሚገባ ምክረ ኃሳባቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም