በደቡብ ክልል በተፈጥሮ አደጋ የተፈናቀሉትን መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ ነው

55
ሃዋሳ ግንቦት 22/2010  በደቡብ ክልል የተለያዩ አከባቢዎች ሊከሰት የሚችለውን የተፈጥሮ አደጋ ለመከላከልና ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ እየሰራ መሆኑን የክልሉ አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ በክልሉ በቅርቡ በተከሰተው የተፈጥሮ አደጋ በተለያየ ጊዜ ከ37 በላይ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጋንታ ጋማአ ለኢዜአ እንደገለጹት በበልግ ወቅት የጎርፍ፣ የናዳና የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ከብሄራዊ ሜትሪዮሎጂ የደረሰውን ጥቆማ መሠረት በማድረግ የቅድመ መከላከል ስራ ሲከናወን ቆይቷል፡፡ በደረሰ ጥቆማ መሠረትም በክልሉ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ጋሞጎፋ ስልጤ፣ ሃላባ፣ ጉራጌና የክልሉ ደጋማ አካባቢዎችም  የስጋት ቀጠና መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ከክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ማሽነሪዎችን በመከራየትና በሰው ሃይል በእነዚሁ አካባቢዎች የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮች መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡ አስቸጋሪ በሆኑት አንዳንድ ዞኖች ደግሞ ነዋሪዎችን የማስወጣት ተግባር የተከናወነ ሲሆን ከወላይታ ዞን 340፤ ከሲዳማ ዞን ጭሬ ወረዳ ደግሞ 80 አባወራዎችን ወደ ሌላ ስፍራ የማዛወር ስራ መከናወኑን ገልፀዋል፡፡ ማስተባበሪያው ከቅድመ መከላከል በተጨማሪ አስቸኳይ ምላሽ የመስጠትና መልሶ የማቋቋም ስራ እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በክልሉ በሚገኙ በወላይታ፣ ሲዳማ፣ ጋሞ ጎፋ፣ ሀዲያ፣ ስልጤ፣ ጉራጌ ዞኖችና ሀላባ ልዩ ወረዳ በናዳ ፣ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት የተጠቁ ሲሆን በደራሽ ውሃ ለጉዳት የተዳረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ እስከአሁን በክልሉ በተከሰተው የተፈጥሮ አደጋ ከጋሞጎፋ ዞን ዳራማሎ ወረዳ ዘጠኝ፣ ከሲዳማ ዞን ጭሬ ወረዳና ምዕራብ አርሲ ዞን 23 ፣ ከስልጤ ደግሞ 5 ሰዎች በአጠቃላይ የ37 ሰዎች ህይወት ማለፉን ተናግረዋል፡፡ ወደ 30 የሚጠጉ ሰዎች ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና በመከታተል ላይ ናቸው፡፡ በአደጋው ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ምግብና የቤት ቁሳቁስ እንዲሁም የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለዚህም የክልሉ መንግስት 150 ሚሊዮን በላይ ብር የመደበ ሲሆን እስከአሁን ለተከናወነው ስራ 50 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ኮሚቴ መዋቀሩንና ነዋሪዎችን ከስጋት ነፃ ወደሆኑ ቦታዎች የማዛወር ስራ ለመስራት እንደታሰበም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም