የኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማህበር 17 አምቡላንሶችን ለኦሮሚያ ክልል አስረከበ

94

አዳማ የካቲት 30/2011 በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የኦሮሚያ ክልል ማስተባበሪያ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዛቸውን  17 አምቡላንሶችን  ለክልሉ ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች አስረከበ።

አምቡላንሶቹን የተረከቡት ሰባት የከተማ አስተዳደሮችና አስር ወረዳዎች ናቸው፡፡

በአዳማ ከተማ ዛሬ በተከናወነው የርክክብ ስነስርዓት ወቅት በኦሮሚያ ክልል የቀይመስቀል ማህበር የቦርድ ተወካይ አቶ ዳውዲ ሙሜ እንደገለጹት ማህበሩ በክልሉ 108 ማዕከላትና 19 ዞኖች የተሟላ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

በዚህም  በተለይ  የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ  ማህበሩ የበኩሉን  አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ  አመልክተው አምቡላንሶቹ ለህብረተሰቡ  ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ  ማዘጋጃ ቤቶችና ወረዳዎች በቂ በጀት በመመደብ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

" አምቡላንሶቹ  ለታለመለት ዓላማ ብቻ መዋል አለብን " ያሉት አቶ ዳውዲ ለዚህም የክትትልና የቁጥጥር ሥራ በተጠናከረ መልኩ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ማህበሩ ቀልጠፋ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ እንዲረጋገጥ እስካሁን ከ120 በላይ አምቡላንሶችን  ከቀረጥ ነፃ በማስገባት ለህብረተሰቡ አገልግሎት ማከፋፈሉን የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የኦሮሚያ ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ ሙሐመድ ጀማል ናቸው።

አምቡላንሶች በየወሩ ከ150 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወላድ እናቶችና በፅኑ ለታመሙ ዜጎች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም ተናግረዋል።

አቶ ሙሐመድ እንዳሉት ማህበሩ 17 የመድኃኒት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በ19 የኦሮሚያ ዞኖች በመክፈት በአነስተኛ ዋጋ ደረጃውን የጠበቀ መድኃኒት ህዝቡ እንዲያገኝ እየሰራ ነው፡፡

በተጨማሪም በኦሮሚያም ሆነ አጎራባች ክልሎች ተፈናቅውለው የመጡ ወገኖች ማህበሩ ከ108 ሚሊዮን ብር በላይ  የሚገመት የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉንም አመልክተዋል።

በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ በኩል ተገዝተው በወረዳዎች አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ከ700 በላይ አምቡላንሶች ለክልሉ ቀይመስቀል ተሰጥተው ዘላቂና አስተማማኝ አገልግሎት  መስጠት እንዲችሉ ከመንግስት ጋር መግባባት ላይ መድረሳቸውንም አስታውቀዋል።

ይህም በአምቡላንሶች  ፈር የለቀቀ የኪራይ ሰብሳቢነትና ያልተገባ አገልግሎት ላይ ማዋልን ከመሰረቱ ለማስቀረት እንደሚረዳ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም