የተቀናጀ የመሬት ይዞታ አስተዳደር ስርዓት በ23 ከተሞች ተግባራዊ ሊደረግ ነው

59

ሀዋሳ የካቲት 30/2011 የተቀናጀ የመሬት ይዞታ አስተዳደር ስርዓት በ23 የሀገሪቱ ከተሞች ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን የከተማ፣ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ።

ስርአቱ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሃዋሳ ከተማ በመተግበር ላይ መሆኑም ተመልክቷል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ ጃንጥራር አባይ በሃዋሳ የይዞታ ምዝገባና አስተዳደር ስርዓት አተገባበሩ ያለበትን ደረጃ  ቃኝተዋል።

ሚኒስትሩ በእዚህ ውቅት እንዳሉት ባህር ዳር፣ መቀሌና አዳማን ጨምሮ በ23 የሀገሪቱ ከተሞች ስርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ ቅድመ ሁኔታዎች  ተጠናቀዋል።

" ስርዓቱ ለባለ ይዞታው የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት መስጠት ብቻ ሳይሆን በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት " ያሉት ሚኒስተሩ የከተማ መሬትና ቦታ ለምን ጥቅም እንደዋለና በምን መልኩ እንደለማ ለማወቅ እንደሚያስችልም አመልክተዋል።

በባለይዞታዎች መካከል የሚነሳ የወሰን ውዝግብና ሌሎች መሰል ችግሮች እንዲፈቱና ባለይዞታው የሚፈልገውን አገልግሎት በቀላሉ ማግኘት እንዲችል የሚያግዝ መሆኑንም አስረድተዋል።

"ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በቀላሉ ለመለየትና ለመፍታትም ያስችላል" ብለዋል።

" በሃዋሳ የተጀመረው የተቀናጀ የመሬት ይዞታ አስተዳደር ስርአት አበረታችና ጅምሩም በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል" ብለዋል ።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ክፍሌ ገብረማርያም በከተሞች ከመሬት ልማትና አስተዳደር ጋር ተያይዘው የሚነሱ ሮሮዎች መበራከታቸውን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት ሥራውን የሚያከናውን አደረጃጀት ከመፍጠር ጀምሮ የህግ ማዕቀፍ በማውጣት የህዝቡን ሮሮ ለማስቀረት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

አቶ ክፍሌ እንዳሉት በክልል ደረጃ የመሬት ምዝገባና የመረጃ ኤጀንሲ ተቋቁሞ የመሬት ምዝገባ ሥራው ሃዋሳ ከተማን ጨምሮ በአምስት የክልሉ ትላልቅ ከተሞች ተጀምሯል።

" ምዝገባው በክልሉ ያለውን የመሬት ሀብት በትክክል አውቆ ለማስተዳደርና መንግስት ሊያገኘው የሚገባውን ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ ያስችላል " ብለዋል።

ከመሬት ሀብት ጋር ተያይዞ የሚነሱ የኪራይ ሰብሳቢነትና የሌብነት ተግባራትን ለመከላከል እንደሚያግዝም ነው የጠቆሙት።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለመዝጋቢ ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን አቶ ክፍሌ ተናግረዋል።

በመሬት ልኬታና ምዝገባ ላይ የተዘጋጀውን ስልጠና ከወሰዱ ባለሙያተኞች መካከል ከወላይታ ሶዶ ከተማ የመጡት ወይዘሮ ለምለም ከበደ ይገኙበታል።

ምዘገባው በኮምፒውተር የተደገፈና ዘመናዊ ስርዓት ያለው መሆኑ ከሰነድና ከመረጃ ጋር ተያይዞ የሚነሱ የህዝብ ቅሬታዎችን ያስቀራል የሚል እምነት እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።

ለሁለት ሳምንት የተሰጠውን ስልጠና ላጠናቀቁ ባለሙያዎችና በአዲሱ የምዝገባ ስርአት ይዞታቸውን ላስመዘገቡ ነዋሪዎች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም