የለውጥ ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ በጋራ መስራት ይገባል ---ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር

73

ባህርዳር የካቲት 30/2011 በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ችግሮችን በማስተካከል በጋራ መስራት እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀድሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር  አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሽኝት ፕሮግራሙ ላይ በተገኙበት ወቅት እንዳሉት አሁን በሃገሪቱ እየተስተዋለ ያለው የለውጥ ተስፋ በብዙ መስዋትነት ተከፍሎበት የመጣ ነው፡፡

"ለውጡ ያስገኛቸውን ድሎች አለማድነቅና እውቅና አለመስጠት ንፉግነት ቢሆንም በለውጡ ስኬታማ ጉዞ በመርካት መዘናጋት የዋህነት ነው" ብለዋል፡፡

ችግሮችን አስተካክሎ ሂደቱን በአስተውሎትና ብስለት በተሞላበት መንገድ በመምራት የለውጡን ዘላቂነት ማረጋገጥ አመራሩና ህዝቡ በጋራ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የትግሉና የለውጡ ከፍታ የሚለካውም በጊዜያዊ ብሶቶች ሳይሆን በመርህ ላይ በመቆም የሃገሪቱን ክብር ለማስጠበቅ በአሸናፊነት እርካብ ላይ በመውጣት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በሽኝት ፕሮግራሙ  የተገኙት  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው "ህዝብንና ሃገርን በምንመራባት የስልጣን ዘመን ከፀፀት የፀዳ እንዲሆን ሰላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን በመስበክ ለህሊና ተገዥ ሆኖ መስራት ይገባል " ብለዋል፡፡

በየዕለቱ  የሚገጥሙ ፈተናዎችን በከፍተኛ ጀግንነት ተጋፍጦ በማሸነፍ ትውልድን አዲስ ታሪክ ፅፎ ማሻገር የኃላፊነት ግዴታ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

"አሁን የገጠሙን ችግሮች በጠንካራ ትግል የሚፈቱ እንጂ ጉዟችን የሚያቆሙ አይደሉም " ሲሉም  ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ህዝብ የትናንት ጀግንነቱን እንዲደግም ዛሬን በይቅርታና በአርቆ አሳቢነት ከሌሎች ህዝቦች ጋር ተባብሮና ተደጋግፎ መቀጠል እንዳለብትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የክልሉ  ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን  በክልሉ ሰላምን የማስከበርና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባር  ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

"በተለይም በአሁኑ ወቅት የገጠሙ ፈተናዎችን ከህዝብ ጋር ሆኖ በብስለት በመምራት አመርቂ ውጤት ለማምጣት እንተጋለን " ብለዋል፡፡

የቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው "ታላቁን የአማራ ህዝቦች መምራቴ ኩራት ይሰማኛል " ብለዋል፡፡

በስልጣን በቆዩበት አምስት ዓመታት ስራዎቻቸው የተሳኩ እንዲሆን በመምከርና በማገዝ ድጋፍ ላደረጉላቸው ሁሉ አመስግነዋል፡፡

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በአመራርነት ቆይታቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልመዋል፤ ሽኝትም ተደርጎላቸዋል፡፡

በሽኝት ፕሮግራሙ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ ባለሃብቶች፣ ወጣቶችና ሴቶች ተካፋይ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም