የኢቦላ ወረርሽኝ የኢትዮጵያ ስጋት እንዳይሆን የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየተከናወኑ ነው

56

አዲስ አበባ ካቲት 30/2011 የኢቦላ ወረርሽኝ የኢትዮጵያ ስጋት እንዳይሆን የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን ተናገሩ።

የኢቦላ በሽታ በቅርቡ በዲሞክራቲክ  ሪፐብሊክ ኮንጎ በድጋሚ ተከስቶ ከ200 በላይ ዜጎች መሞታቸውና ይህም ተባብሶ ይቀጥላል የሚል ስጋት እንዳላቸው የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ዘግበዋል።  

ደቡብ ሱዳንም ይሄንን ተከትሎ ወረርሽኙ በቅርቡ ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት እንዳደረባትና የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎችን እያከናወነች መሆኑን መግለጿ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ወረርሽኙ በዲሞክራቲክ  ሪፐብሊክ ኮንጎ  በድጋሚ ተቀስቅሷል ከተባለበት ግዜ ጀምሮ ጠንካራ የሆነ የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝና ችግሩ እንደማያሰጋት የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር ለኢዜአ ተናግረዋል።

በአገሪቱ ለህብረተሰቡ የጤና ስጋት የሆኑትን ተላላፊ በሽታዎች ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችልና በተለይም የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በሙሉ አቅሙ የሚያከናውን ኤጀንሲ ተቋቁሞ ስራዎች እተከናወኑ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ኢቦላ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የህክምና ባለሙያዎችን በመላክ ድጋፍ ማድረጓን ያስታወሱት ዶክተር አሚር አገሪቱ የመከላከል ስርአት በመገንባቷ በአለም የጤና ድርጅት እውቅና እንድታገኝ እንዳስቻላት ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኢቦላ በመከሰቱ ለኢትዮጵያ ስጋት እንዳይሆን የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጨምሮ በተለያዩ 30 የድንበር ኬላዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎች ቅድመ ምርመራ እየተደረገላቸው መሆኑን ነው የጠቆሙት።

ወረርሽኙ በቀጣይም የኢትዮጵያ ስጋት እንዳይሆን ለማድረግም የቅድመ ምርመራውና የመከላከል ስራው ያለማቋረጥ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

አለም ዓቀፉ የጤና ድርጅት የኢቦላ ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ ጠንካራ ዝግጁነት አሳይተዋል በሚል እውቅና የሰጣቸው የአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያንና አልጄሪያ ብቻ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም