የእንስሳት ጤና አገልግሎት ሊጠናከር ይገባል...በጋምቤላ አርብቶ አደሮች

123

ጋምቤላ  የካቲት 30/2011 በጋምቤላ ክልል የላሬና የኢታንግ ልዩ ወረዳ አርብቶ አደሮች ለእንስሶቻቸው የሚሰጠው የጤና አገልግሎት እንዲጠናከር ጠየቁ።

የክልሉ እንስሳትና ዓሣ ሀብት ቢሮ በበኩሉ የእንስሳት የጤና አገልገሎትን በማሻሻል አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በላሬ ወረዳ ንብንብ ቀበሌ የቀንድ ከብቶቻቸውን ሲያስከትቡ ከነበሩት አርብቶ አደሮች መካከል አቶ ጀምስ ቱት በሰጡት አስተያየት ከብቶቻቸው በተለይም በክርምት ወራት ለተለያዩ በሽታዎች እየተጋለባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ እንስሳት ጤና ተቋም በመሄድ የመድኃኒት ጥያቄ ሲያቀርቡ መድኃኒት የለም የሚል ምላሽ እንደሚሰጣቸውና በእዚህም ከብቶቻቸው  ለሞት እየተዳረጉባቸው መሆኑን ነው የገለጹት።

በክርምት መግባያና መውጫ ወቅት ከብቶቻቸው በተለይ አንገታቸው አካባቢ እያበጠ እንደሚታመሙባቸው የገለጹት ደግሞ የዚሁ ቀበሌዋሪ አርብቶ አደር ፒታር ዳክ ናቸው።

መንግስት የእንስሳት ጤና አገልግሎቱን በማሻሻል ከቀንድ ከብተቻቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል።

በኢታንግ ልዩ ወረዳ የዋትጋች ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጋትቤል ማጆክ በበኩላቸው በአካባቢያቸው በቂ የእንስሳት መድኃኒት አቅርቦት ባለመኖሩ በችግር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

'' ከሃምሳ በላይ የቀንድ ከብቶች ቢኖሩኝም በአካባቢው የመድኃኒት አቅርቦት ባለመኖሩ ከብቶች እየተጎዱብኝ ነው፣ በመሆኑም በመንግስት በኩል መድኃኒት ሊቀርብልን ይገባል።

የክልሉ እንስሳትና ዓሣ ሃብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋልዋክ ዎል ስለጉዳዩ ተጠይቀው ከእንስሳት መድኃኒት አቅርቦት ጋር ተያይዞ ከአርሶአደሮቹ  የቀረበው ቅሬታ ትክክለኛ መሆኑን ተናግረዋል። 

የአርብቶ አደሮቹን የእንስሳት ጤና አገልግሎት ችግር ለመፍታት ቢሮው በአዲስ መልክ ተደራጃቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደኃላፊው ገለጻ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች ድንበር ዘለል የቀንድ ከብት በሽታዎችን ለመከላከልና የእንስሳቱን ጤና ለማሻሻል ክትባት በዘመቻ መልክ እየተሰጠ ነው ።

በቢሮው የእንሳሳት ጤና አጠባባቅ የሥራ ሂደት ባለቤት ዶክተር አካሉ ከበደ በበኩላቸው ከእዚህ በፊት በነበረው የቢሮ አደረጃጀት አርብቶ አደሩ ተገቢውን የእንስሳት ጤና አገለግሎት ሳያገኝ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት ቢሮው በተሻለ መልክ በመደራጃቱ ለአርብቶ አደሩ የተሻለ የእንስሳት የጤና አገልግሎት ለመስጣት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በእዚህም ከ315 ሺህ ለሚበልጡ የዳልጋ ከብቶች ከየካቲት 27 ቀን 2011 ጀምሮ የጉሮርሳ በሸታ መከላከያ ክትባት በዘመቻ መልክ እየተሰጠ መሆኑን ነው የገለጹት።

"በቅርቡም የበግና የፍየል በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል ክትባት በተመሳሰይ መልኩ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው" ሲሉ ዶክተር አካሉ ተናግረዋል።

በጋምቤላ ክልል 1 ሚሊዮን የሚጠጋ የቀንድ ከብት ይኖራል ተብሎ እንደሚገመት ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም