አራተኛው የህዝብና ቆጠራ ከውጤት በኋላ ቅሬታ እንዳይነሳበት ተገቢው ቅድመ ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል

170

አዲስ አበባ የካቲት 30/2011 አራተኛው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት ሲገለጽ ቅሬታ እንዳይነሳበት ትክክለኛና ተዓማኒነት ያለው መረጃ ለመሰብሰብ ተገቢው ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ ታዋቂ ግለሰቦች አሳሳቡ።

በሶስተኛው የህዝብና ቤቶ ቆጠራ ውጤት ላይ የተለያዩ ወገኖች ቅሬታ እንደነበራቸው ያስታወሱት የብሔራዊ የዕርቅ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ የፊታችን መጋቢት 29 ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ቆጠራ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ቆጠራው ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተካሂዶ በማንኛውም ሰው ቢፈተሽ ተመሳሳይ የሆነ ውጤት በሚሰጥ መልኩ መካሄድ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

ህዝቡ በቆጠራው ሂደት 'ያጋጥማሉ' ብሎ የሚያስቀምጣቸው ስጋቶች ተለይተው ከወዲሁ መፍትሄ እንዲሰጣቸው አመልክተዋል።

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩሉ ቅሬታ የማያስከትል እንዲሆን ለማድረግ በቆጠራው ትክክለኛ መረጃ ለማሰባሰብ የማዕከላዊ ስታቲክስ ኤጀንሲ፣ የተለያዩ የህብረተሰብ አካላትና ሕብረተሰቡ በጋራ ሀላፊነታቸውን በመወጣት እንዳለባቸው አመልክቷል።

ህብረተሰቡም ውጤቱ ሲገለጽ ቅሬታ ከማቅረብ ይልቅ በሂደቱ የድርሻውን በመወጣት ትክክለኛ ስራ ለመስራት የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እንዳለበት አመልክቷል።

የእስልምና መጻህፍት ፀሀፊ የሆኑት አቶ አህመዲን ጀበል በቆጠራው ወቅት ስህተቶች እንዳይፈጠሩና  የተሰበሰበው ትክክለኛ መረጃ ውጤት ይፋ ሲደረግ ጥንቃቄ መወሰድ እንዳለበት ይናገራሉ።

አቶ አህመድ እንደገለጹት፤ ትክክለኛ የሆነ የህዝብና የቤቶች ቆጠራ ጥቅሙ ምን እንደሆነ ማስገንዘብ ላይ መሰራት ይኖርበታል።

ሕብረተሰቡ በእያንዳንዱ የቆጠራ መስፈርት የትምህርት ደረጃ፣ የኑሮ ሁኔታ፣ የስራ አጥ ቁጥር፣ ብሄር፣ ሀይማኖትና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ መስጠት እንደሚገባም ገልጸዋል።

የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ ተዓማኒነት ያለውና ትክክለኛ የህዝብና የቤት ቆጠራ ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ብቃትና ስነ ምግባር ያላቸውን የቆጠራ ባለሙያዎች መልመልና ማሰልጠን፣ የቆጠራ መሳሪያ ቴክኖሎጂዉን መፈተሽ፣ ከክልሎች ጀምሮ ታች ድረስ ካሉ መዋቅሮች ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ከተከናወኑ ስራዎች መካከል ጠቅሰዋል።

እንደ አቶ ቢራቱ ገለጻ፤ ኤጀንሲው ትክክለኛ ቆጠራ እንዲከናወንና ውጤቱ ከፖለቲካ ተጽዕኖ ነጻ እንዲሆን የክትትል ስርዓት አዘጋጅቷል።

የህዝብና ቆጠራ ማካሄድ የዜጎችን ትክክለኛ ፍላጎት ለይቶ ለመስራት የሚያስችል መነሻ ነው።

የአገሮች የልማት ፖሊሲና ዕቅድ ሲነደፍ የህዝብን ቁጥር መሰረት በማድረግ በመሆኑ ለቆጠራ ሂደትና ትክክለኛ ውጤት መምጣት ተገቢውን ጥንቃቄ ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም