ለተሻለ ልማት ከተሞች ገቢያቸውን ማጠናከር አለባቸው… የደቡብ ክልል

203

ሆሳዕና የካቲት 30/2011 በደቡብ ክልል የሚገኙ ከተሞች የገቢ አሰባሰብ ስርዓታቸውን በማጠናከር የተሻለ ልማት ማስመዝገብ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ፡፡

የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ በሆሳዕና ከተማ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ በ2011 የመጀመሪያው ግማሽ የበጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸሙን በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ  አስቀምጧል፡፡ 

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የቢሮው ኃላፊ  አቶ ክፍሌ ገብረ ማርያም በዚህ ወቅት የከተሞች ገቢ አሰባሰብ ውስንነት ለልማቱ ማነቆ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

" ገቢ ለከተማ እድገት ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ገቢ ባልተሰበሰበበት እድገት የለም" ብለዋል፡፡

የራስን አቅም በራስ መሸፈን ለከተሞች እድገት የጎላ ፋይዳ እንዳለው ያመለከቱት  አቶ ክፍሌ  ከተሞች የገቢ አሰባሰብ ስርዓታቸውን በማጠናከር የተሻለ ልማት ማስመዝገብ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የከተሞች እድገትና መስፋፋት ፍጥነት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው  በማዕከላዊ ስታስቲክስ መረጃ እውቅና ያገኙ የክልሉ ከተሞች ብዛት 445 መድረሱንና የከተሜነት ምጣኔ 7 በመቶ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

" ከተሞች ለነዋሪው  ምቹ እንዲሆኑ ከማዘጋጃ ቤቶች የሚሰበሰብ ገቢ ያለዉ ድርሻ ከፍተኛ ነው" ብለዋል፡፡

በአለም ባንክ ብድር ተጠቃሚ የሆኑ ከተሞች ገቢ ባልሰበሰቡት መጠን ለከተሞች እድገት አሉታዊ ተፅእኖ ከመፍጠር ባሻገር ከተማው የሚጠበቅበትን ገቢ ባለመሰብሰብ ቅጣት እንደሚጣልበትም ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድማገኝ ደግፌ በበኩላቸው " ከተሞች በአስተማማኝ መልኩ ገቢያቸውን በመሰብሰብ የአካባቢያቸውን ልማት ማጠናከር ይኖርባቸዋል" ብለዋል፡፡

ከተሞች በተለየ መልኩ ከማዘጋጃ ቤት  የተሻለ ገቢ ሊያስገኝ የሚችለውን ቀጥተኛ ያልሆነውን የተጨማሪ እሴት ታክስ ገቢ አጠናከረው በመሰብሰብ በከተሞች የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡

ከውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ከጊዶሌ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት የመጡት  አቶ ዋሰይሁን ታዬ የከተማ ልማት ተግባር የሆነውን ቤትና ቦታን ለማቅረብ ለባለይዞታዎች የካሳ ክፍያ አስፈላጊ  መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህንንም ክፍያ ለመፈጸም በከተሞች ገቢን አጠናክሮ መሰብሰብ አማራጭ የሌለው ተግባር እንደሆነም ጠቁሟል፡፡

"  እንደ ጊዶሌ ከተማ አስተዳደር ያለብንን የገቢ የአሰባሰብ ችግር በመቅረፍ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት እንሰራለን" ብለዋል፡፡

ለመሰረተ ልማት ስራዎች ተደራሽነት ገቢ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት  ደግሞ ከኮንሶ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የተሳተፈው አቶ ገዛኸኝ ካንታዬ ነው፡፡

ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ያልሆኑ ገቢዎችን ትኩረት ሰጥቶ በመሰብሰብ የከተማ ልማት ስራዎች ማፋጠን አማራጭ የሌለው መንገድ እንደሆነም ተናግሯል፡፡

በፕላን ዝግጅትና አተገባበር  ክፍተቶች፣ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አሰጣጥ፣ የገቢ አሰባበስብና ለማህበራት የመሬት አቅርቦት በመድረኩ በእጥረት ተገምግመዋል፡፡

የገቢ አቅምን ማሳደግና አረንጓዴ ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ ደግሞ የቢሮው ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው ተብለዋል፡፡

በመድረኩ ከሁሉም የክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መስሪያ ቤቶች የተወጣጡ የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ተሳትፈዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም