ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የተመድ ረዳት ዋና ጸሀፊ ሆነው ተሾሙ

63

አዲስ አበባ የካቲት 29/2011 የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ጸሀፊ ሆነው ተሾሙ።

የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ለዚህ ከፍተኛ አለምዓቀፍ ኃላፊነት ዶክተር ወርቅነህን መሾማቸውን ዛሬ ይፋ አድርገዋል።

ዶክተር ወርቅነህ በድርጅቱ ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ የተሾሙት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ባደረገችው አስተዋጽኦ እንዲሁም እርሳቸው ለድርጅቱ ዘላቂ የልማት ግቦች መሳካት በተጫወቱት የመሪነት ሚና መሆኑም ታውቋል።

ሚኒስትሩ መቀመጫውን ናይሮቢ ኬንያ ያደረገ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር የሚገኙ 18 ኤጀንሲዎችን የማስተባበር ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

ይህ ሹመት ኢትዮጵያ ለባለብዙ ወገን ላደረገችው አስተዋጽኦ የተሰጠ እውቅና መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።   

ከጠቅላይ ሚኒስተር ፅህፈት ቤት ቲውተር ገፅ የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በአንቶኒዮ ጉተሬዝ በመሾማቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የእንኳን ደስ አሎት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ዶክተር ወርቅነህ በተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የኃላፊነት ቦታዎች አገራቸውን  ከ20 አመት በላይ ያገለገሉ ሲሆን  አሁን ላለው ለውጥ ሚናቸው የጎላ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም