በሰሜን ሸዋ ዞን ሞዴል ሴት አርሶ አደሮች ተሸለሙ

62

ደብረብርሀን የካቲት 29/2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተደረገላቸው ጠንካራ የግብርና ኤክስቴንሽን ድጋፍ እስከ አምስት ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 45 ሞዴል ሴት አርሶ አደሮች ተሸለሙ፡፡

የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድ ወሰን አድማሴ በሽልማቱ ስነስርዓት ወቅት እንዳሉት ከ273 ሺህ በላይ ሴቶች በግብርና ኤክስቴሽን ታቅፈው ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡

ተሸላሚ ሴት ሞዴል አርሶ አደሮች በግብርና ኤክስቴንሽን ታቅፈው የስልጠና፣ የብድርና የተሻለ ሙያዊ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡

የተሰጣቸውን የባለሙያ ምክረ ሃሳብ በመተግበር የተሻለ ምርት በማግኘትና በተሻለ ደረጃ በመቆጠብ ሃብት ሊያፈሩ ችለዋል፡፡

አሁን ለሽልማት የበቁት ሴቶች በተደረገላቸው ድጋፍ የግል ጥረታቸውን ጨምረው ከሁለት እስከ አምስት ሚሊዮን ብር ሃብት ማፍራት የቻሉ ሞዴሎች መሆናቸውን አቶ ወንድ ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ በርሃኑ ታየ በበኩላቸው ተሸላሚዎች በቀጣይ ምርትን በብዛትና በጥራት አምርተው  ለኢንዱስትሪዎች በማቅረብ በሞዴልነታቸው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ሴቶች በተሰማሩበት የስራ መስክ ውጤታማ  ሆነው ለሌሎች ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር የጀመሩትን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡

" ሴቶች ከማህበራዊ ጫና ተላቀው በልማት ጠንካራና ሞዴል መሆን የድርብ ጀግንነት ነው " ያሉት አቶ ብርሃኑ በቀጣይም ለተሻለ ድል መትጋት እንደሚገባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በእንሳሮ ወረዳ የወቀሎ ቀበሌ ሞዴል ሴት አርሶ አደር ወይዘሮ አበበች በቀለ በሰጡት አስተያይ  ከአስር ዓመት በፊት ከመሬታቸው የሚያገኙት የምርት መጠን በዓመት ከ10 ኩንታል እንደማይበልጥ ተናግረዋል፡፡

በግብርና ኤክስቴሽን በመታቀፍ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ እንዲሁም የባለሙያ ምክረ ሃሳብ ተጠቅመው  ለገበያ የሚቀርብ በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከእርሻ ስራቸው ጎን ለጎን በወተት ላሞችንና ዶሮ  እርባታ በመሰማራት የተሻለ ገቢ እያገኙ ባፈሩት ሀብት ጭምር ሲኖትራክ የጭነት መኪና እና የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በመግዛት ውጤታማ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ 

በሞረትና ጅሩ ወረዳ የማንጉዶ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ወይዘሮ አበራሽ በሻህ ውረድ በበኩላቸው ስንዴ፣ ጤፍና ምስር በዘመናዊ ቴክኖለጂን ተጠቅሞ በመዝራት በዓመት 80 ኩንታል እየመረቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የእህል ወፍጮ ተክለው ገቢ እንደሚያገኙ ጠቅሰው  በቅርቡም ግብርናቸውን ለማዘመን በ370ሺህ ብር የእህል መውቂያ ማሽን መግዛታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

" የመኖሪያ ቤት አለኝ በአዲስ አበባም ግምቱ 1ሚሊየን ብር የሚያወጣ ቤት ገዝቻለሁ " ያሉት ወይዘሮ አበራሽ አሁን ላይ የተጣራ ካፒታል 4ሚሊየን ብር የሚጠጋ  ሀብት እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡

" ሴት ልጆች ከአረብ ሀገር ስደት ተቆጥበው እኛን በመመልከት በሀገራቸው መለወጥ ይችላሉ " ያሉት ደግሞ የአፆኪያና ገምዛ ወረዳ ሴት አርሶ አደር ማሜ ጥላሁን ናቸው፡፡

ከባለሙያዎች ባገኙት ምክረ ሀሳብ በአትከልትና ፍራፍሬ ልማት በመሳተፍ እንዲሁም ከመደበኛው  እርሻ ዓመታዊ ገቢያቸዉን ከ200 ሺህ ብር በላይ ማሳደግ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

የተደረገላቸው የዋንጫ፡ የምስክር ወረቀትና የሞባይል ሽልማትም የሚያበረታታና ልምዳቸውን ለሌሎች ለማስተላለፍ እንዳነሳሳቸው ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም