የፓርላማ መንደሩ ግንባታ የከተማ አስተዳደሩ ከጀመረው የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር ጋር አይጋጭም -አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

53

አዲስ አበባ የካቲት 29/2011 በአዲስ አበባ የሚገነባው የፓርላማ መንደር የከተማ አስተዳደሩ ከጀመረው የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር ጋር የማይጋጭ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለፀ።

የፌደሬሽንና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶችን በአንድ ላይ የያዘ የፓርላማ መንደር በ4 ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የዲዛይን ጥናት እየተደረገ ነው።

አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እንዳሉት፤ ለሁለቱም ምክር ቤቶች የሚገነባው የፓርላማ መንደር ዘመናዊና ባለሙያዎች የፈለጉትን መረጃ በቀላሉ ማግኘት የሚያስችላቸው ነው።

የፓርላማ መንደሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከጀመረው የወንዝ ዳርቻዎችን በአረንጓዴ እጽዋት የማስዋብ መርሃ ግብር ጋር የማይጋጭ መሆኑን ገልጸዋል።

ግንባታው ከአረንጓዴ ልማት ጋር የተሳሰረ መሆኑን የገለጹት አፈ ጉባኤ ታገሰ፤ ለዚህ ደግሞ ከከተማ አስተዳደሩና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እውን ይሆናል ብለዋል።

የዲዛይንና የአፈር ጥናት ስራው በመጠናቀቁ ዲዛይኑ በባለሙያዎች ተገምግሞ በቀጣይም ዓመት ግንባታው እንደሚጀመር ገልጸዋል።

ማንኛውም የግንባታ ሂደት የከተማዋን ውበት ታሳቢ ያደረገ መሆን ስላለበት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በተናበበ መልኩ ይከናወናል ብለዋል።

አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የምክር ቤቱን የ2011 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የስራ አፈጻጸምን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ የኅብረተሰቡን ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስና የተጀመረው ለውጥ ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አደረጃጀት መፈጠሩን ተናግረዋል።

የቋሚ ኮሚቴዎችን ቁጥር ከ 21 ወደ 10 ዝቅ በማድረግ ሰብሳቢዎቹም በምክር ቤቱ እንዲሰየሙ ተደርጓል።

በዚህም መሰረት በስድስት ወራት ስምንት ተጠሪ መስሪያ ቤቶችን በቀጥታ 130 ተቋማትን በቋሚ ኮሚቴዎች አማካኝነት ገምግሞ ግብረ መልስ መስጠቱንም አክለዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት የህብረተሰቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ 26 ረቂቅ አዋጆች ለምክር ቤቱ ቀርበው እንዲጸድቁ መደረጉንም ጠቁመዋል።

የምክር ቤቱ አባላት የአስፈፃሚ አካላትን እንቅስቃሴ በመስክ ምልከታ ገምግመዋል ያሉት አፈ-ጉባኤው  በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰቱ ችግሮች ከህብረተሰቡና ከመንግስት አቅም በላይ አለመሆናቸውን ገልፀዋል። 

በኢትዮጵያ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉና በተለያዩ ሁኔታዎች አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የተከናወኑ ተግባራት ያሉ ቢሆንም ውስንነት ስላለ ከዚህ በላይ መስራት ይጠበቃል ብለዋል።

በተጨማሪም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው አራተኛው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ኮሚሽን የተጓደሉ አባላትን ከማሟላት ጀምሮ በቂ ዝግጅት እንደተደረገበትም ተናግረዋል።

ቆጠራው ለቀጣይ እቅዶች አስፈላጊ በመሆኑም ለስኬታማነቱ ተገቢው ጥንቃቄና ክትትል እንደሚደረግ ገልጸው፤ ህዝቡም በየአካባቢው ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም