ባህር ዳር ማረሚያ ቤት የተነሳ ግጭት የህይወትና የአካል ጉዳት አስከተለ

79

ባህርዳር የካቲት 29/2011 በባህር ዳር ማረሚያ ቤት ዛሬ የተቀሰቀሰ ግጭት የህይወትና የአካል ጉዳት ማስከተሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የከተማው ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ውብሸት መኮንን ለኢዜአ እንደገለፁት ችግሩ የተከሰተው ዛሬ ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ተኩል አካበቢ ነው።

በአንድ የማረሚያ ክፍል በስውር የገባ እቃ ለመፈተሽ የጸጥታ አካላት ገብተው የሞባይል ስልክ ቢያገኙም በተወሰኑ ታራሚዎች እንዳይወጡ እገታ ስለተደረገባቸው ግጭቱ መነሳቱን አስረድተዋል።

በግጭቱም ሰባት የጸጥታ አካላትና ከ20 የሚበልጡ ታራሚዎች ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን የሶስት ታራሚዎች ህይወት ማለፉን ገልጸው ተጎጂዎቹ በፈለገ ህይወትና ፈለገ ጥበብ ሆስፒታሎች ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት የተረጋጋ ሁኔታ መፈጠሩን ኮማንደር ውብሸት አስታውቀው፤ የበለጠ የማረጋጋት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም