የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋም የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መርሃ ግብር ለመተግበር እንቅስቃሴ ተጀመረ

513

አዳማ የካቲት 29/2011 የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋም የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መርሃ ግብር ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተፈጥሮ ሀብት፣መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ከተጠሪ ተቋማት  ጋር  ለመምከር ሚኒስቴሩ ያዘጋጀው  ዓውደ ጥናት ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

በሚኒስቴሩ የመጠጥ ውሃ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ እንዳሉት መርሃ ግብሩ ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ 382 ወረዳዎችን ጨምሮ የመጠጥ ውሃ እጥረት ባለባቸው ደረቃማ አካባቢዎች ትኩረት ተደርጎ የሚከናወን ነው።

ወደ ስራ ለመቀየርም   ድርቅ በተደጋጋሚ የሚያጠቃቸውን አካባቢዎችን  የመለየት ፣ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥ የአምስት ዓመታት መርሃ ግብር ሰነድ ዝግጅት የማጠናቀቅ፣ ሃብት የማፈላለግ ፣የጥናትና የዲዛይን ሥራዎች መጀመራቸውን አመልክተዋል።

የእንግሊዝና የፊንላንድ መንግሥት፣ የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት /ዩኒሴፍ/ እና  የዓለም ባንክ መርሃ ግብሩን በገንዘብ  ለመደገፍ ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቁመዋል።

በአፋር፣ሶማሌ፣አማራ፣ ኦሮሚያ፣ደቡብና ትግራይ ክልሎች የጥናትና ዲዛይን ሥራው በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በሶማሌ ሽንሌ፣ድሬዳዋ፣ሐረርና ጅግጅጋ የመጠጥ ውሃ ኔትወርክ  እና በኦሮሚያ የቦረና ኔትወርክ  ቅድመ ጥናት ሰነድ ተዘጋጅቶ ለፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት ቀርቧል።

ሚኒስቴሩ ለመርሃ ግብሩ ስኬታማነት ከባለ ድርሻ አካላት፣ ከልማት አጋሮችና ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

የውሃ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ባሻህ ሞገስ በበኩላቸው  በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የትግበራ ዘመናት በልማት አጋሮች ከሚደገፉ ፕሮጀክቶች መካከል በስምንት ቢሊዮን 600ሚሊዮን ብር በጀት የተጀመረው የ” ዋን ዋሽ”  መርሃ ግብር አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ እስከ 2011 ዓ.ም. ድረስ በ382 የገጠር ወረዳዎችና ከተሞች አምስት ሚሊዮን 900ሺህ ህዝብ የውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እስካሁን 68 በመቶ መከናወኑን  አስረድተዋል።

መስሪያ ቤታቸው በ104 ከተሞች ለሚካሄዱ የውሃ ፕሮጀክቶች ዘጠኝ ቢሊዮን 800 ሚሊዮን ብር በብድር መስጠቱን የገለጹት ደግሞ የውሃ ልማት ፈንድ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዋና ዋኬ ናቸው፡፡

በከተሞቹ ግንባታቸው ከተጀመረው 114 ፕሮጀክቶች መካከል 34 መጠናቀቃቸውን አመልክተው ቀሪዎች በግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የተጠናቀቁትን ፕሮጀክቶች ጨምሮ ግንባታቸው በሂደት ላይ የሚገኙት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ 8 ሚሊዮን ህዝብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ለሶስት ቀናት የሚቆየው አውደ ጥናቱ በውሃ ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስራ እንቅስቃሴ ዙሪያ ይመክራል፡፡