የስፖርት የጥናት ውጤቶችን ባለድርሻ አካላት ሊጠቀሙባቸው ይገባል ተባለ

45
አዲስ አበባ ግንቦት 22/2010 በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የሚዘጋጁ የምርምር ስራዎችን የስፖርት ባለድርሻ አካላት በአግባቡ ሊጠቀሙባቸው ይገባል ተባለ። አምስተኛው አገር አቀፍ የስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምር ጉባኤ በአዲስ አበባ ስፖርት አካዳሚ እየተካሄደ ይገኛል። በዚህ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንበሳው እንየው በአካዳሚውና በግለሰቦች ፍላጎት ባለፉት አራት ዓመታት 100 ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል። ለአምስተኛ ጊዜ በሚካሄደው የስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምር ጉባኤም 20 ጥናቶች ተሰርተዋል ነው የተባለው። ከእነዚህ ስራዎች መካከል ስፖርትና አመጋገብ፣ የአትሌቶች ጉዳትና ስነ-ልቦና፣ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ያሉባቸው ጫና እና መፍትሄዎቹ የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው። ይሁን እንጂ ጥቂት ክለቦች፣ ተቋማትና ባለሙያዎች ብቻ የምርምር ውጤቶቹን በሚፈለገው መልኩ ጥቅም ላይ  እንዳዋሏቸው አቶ አንበሳው ጠቅሰዋል። ባለድርሻ አካላት እነዚህን ስራዎች በአግባቡ ቢጠቀሙባቸው ለስራቸው የተሻለ ውጤት እንደሚያገኙ በማስገንዘብ። በአምስተኛው የጥናትና ምርምር ጉባኤ በአገሪቱ ወቅታዊ ችግር የሆነው የስፖርታዊ ጨዋነት መንስኤዎችና መከላከያዎቹ በሚል ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመዳሰስ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ መምህር በሆኑት አቶ ተሾመ አጀበው ጥናት ቀርቧል። እንዲሁም በስፖርት ብቃትን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻልና ሌሎችንም የሚዳስሱ ጉዳዮች በመጀመሪያው ቀን ከቀረቡት ውስጥ ይገኙበታል። ከዚህ በተጨማሪ በአካዳሚው በኢትዮጵያ ውስጥ ስፖርቶች በአገር ኢኮኖሚ ላይ ያላቸው ሚና እና የስፖርት አደረጀጃትና አወቃቀርን የሚመለከቱ ጥናቶች እየተካሄዱ ሲሆን በመጪው ዓመት ይጠናቀቃሉ ተብሏል። ጥናቶቹ ተጠናቀው ስራ ላይ ሲውሉ ፖሊሲ  አውጪዎችና የሚመለከታቸው አካላት እንደ ግብአት እንዲጠቀሙበት ይደረጋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም