የጤና ሚኒስቴር በሚያሻሽለው የጤና ፖሊሲ የሴቶችና የወጣቶች አመራርነት ሚና ትኩረት ይሰጠዋል

152

አዲስ አበባ  የካቲት 29/2011 የጤና ሚኒስቴር በሚያሻሽለው የጤና ፖሊሲ የሴቶችና የወጣቶች አመራርነት ሚና ትኩረት እንደሰጠው ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ገለጹ።

ጤና ሚኒስቴር ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ እየተጠቀመበት ያለውን የጤና ፖሊሲ እንደሚያሻሽል መግለጹ ይታወቃል።

ዶክተር አሚር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጤና ዘርፍ ስራ በአብዛኛው የሚከወነው በሴቶች በመሆኑ የአመራነት ሚናቸውም ተመጣጣኝ መሆን አለበት።

በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያሉ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች፣ አዋላጅ ነርሶችና በጠቅላላ የነርስ የህክምና ዘርፎች ሴቶች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ።   

በጤና ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ ሚዛናዊነት ጠብቆ ማስኬድ እንደሚገባ ከስምምነት የተደረሰበት መሆኑን የገለጹት ዶክተር አሚር በሚዘጋጀው የጤና ፖሊሲ ረቂቅ ውስጥ ትኩረት እንደተሰጠው አመልክተዋል።

ተተኪ አመራሮችን ወደ ፊት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥም ከሚኒስቴሩና በዘርፉ ከሚሰሩ ኤጀንሲዎች የተወጣጡ ወጣቶችን ተለይተው ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ የአመራርነት ልምምድ የሚያደርጉበት ስራ ላይ እንደሚመደቡ ተናግረዋል።

ወጣቶቹ በሚመደቡበት ስራ በሚያስመዘግቡት ውጤት መሰረት ወደአመራርነት የሚመጡበት ሁኔታ እንደሚኖር ጠቁመዋል።

ሌላው ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ዩኒቨርሳል ሄልዝ ከቨሬጅ ሚኒስቲሪያል ቻምፒዮን አዋርድ በመጀመሪያ ደረጃ የጤና አጠባበቅ ተሸላሚ መሆኗን ተከትሎ በጤና አጠባበቅ ላይ ለተሰማሩ ሴት የህክምና ባለሙያዎች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።   

እውቅናው እስከ ታች ድረስ ወርዶ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆንና በሽልማቱ ተነቃቅተው የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

የሚሻሻለው ፖሊሲ ተግባራዊ ሲሆን በጤናው ዘርፍ ለሚነሱ ቅሬታዎችና አገልግሎጥ አሰጣጥ ችግሮች ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ፖሊሲው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ችግር በተመለከተ ትኩረት እንደሚሰጥም ተነግሯል።

አዲሱ ረቂቅ የጤና ፖሊሲ በቀጣይ ተከታታይ ውይይቶች ተደርገውበት  ግብአቶች ከተሰበሰቡበት በኋላ ለሚንስትሮች ምክር ቤት የሚቀርብ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም