የአረንጓዴ መዝናኛ አገልግሎት ስራ እራሳቸውን ለመቻል እንደረዳቸው የሽሬእንዳስላሴ ከተማ ወጣቶች ገለጹ

94

ሽሬእንዳስላሴ የካቲት 29/2011 ተደራጅተው የተሰማሩበት የአረንጓዴ የመዝናኛ አገልግሎት ስራ እራሳቸውን ለመቻል እንደረዳቸው በሽሬእንዳስላሴ ከተማ  ወጣቶች ገለጹ

ለወጣቶቹ ከ4 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን የከተማው የወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽህፈት ቤት አመልክቷል፡፡

" ሓየሎም " የአረንጓዴ የመዝናኛ ማዕከል ከሌሎች አምስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ከተሰማሩ ወጣቶች መካከል በሪሁ ተስፋዬ አንዱ ነው።

ወጣቱ  በመዝናኛ ማዕከሉ በሚሰጠው አገልግሎት ከሁለት ሺህ ብር በላይ ወርሃዊ ክፍያ እንደሚያገኝ ለኢዜአ ተናግሯል።

" ያለ ሥራ ለአምስት ዓመታት ተከራትቼያለሁ" ያለው ወጣት በሪሁ፣አሁን በሚያገኘው ገቢ ኑሮውን ለማሻሻል እንደረዳው ገልጿል።

በሽሬ የወጣቶች የአረንጓዴ መዝናኛ ማዕከል እየሰራ  የሚገኘው ወጣት ሰመረ ጎይቶኦም በበኩሉ፣ከሚሰጧቸው የተለያዩ አገልግሎቶችና ከቤት ውስጥ የስፖርት መዝናኛዎች ከሚሰበሰበው ገቢ ተጠቃሚ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ከማዕከሉ  የትርፍ ገቢ በወር  ከሚደርሰው ሌላ  እስከ ሦስት ሺህ ብር ድረስ እንደሚከፈለውና በዚህም እራሱን ለመቻል እንዳገዘው አስረድቷል።

በሚሰጡት አገልግሎት ከሚያገኙት ገቢ  ራሳቸውን መቻላቸውን የተናገረችው ደግሞ  " ሀብቶም" የከተማው የአረንጓዴ የመዝናኛ ማዕከል የምታገለግለው  ወጣት ትርሓስ ሰሎሞን ናት።

" እያንዳንዱ የማህበሩ አባልም በአማካይ በወር ከሁለት ሺህ ብር በላይ ገቢ ያገኛል" ብላለች።

የከተማው የወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ጎይቶኦም ይሰማ በሽሬ እንዳስላሴ 13 አረንጓዴ የመዝናኛ ማዕከላት እንደሚገኙ አመልክተው በእነዚህም 120 ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በማዕከላቱ ውስጥ የተሰማሩ ወጣቶች እያንዳንዳቸው 15 ሺህ ብር አዋጥተው ከገዟቸው የሥራ ቁሳቁሶች በተጨማሪ " ዞአና"  እና " አይ ኦ ኤም"  ከተባሉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከ4 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ግምት ያላቸው ቁሳቁሶች ድጋፍ እንደተደረገላቸው  አመልክተዋል፡፡

ወጣቶቹ አገልግሎታቸውን ለማስፋትም የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ምክርና የድጋፍ ዕገዛ  እየሰጧቸው መሆኑን አቶ ጎይቶኦም  ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም