ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊኖር ስለሚችል በበልግ አብቃይ አካባቢዎች ውሃ ከማሳ የማንጣፈፍ ስራ መስራት ይገባል

482

አዲስ አበባ የካቲት 29/2011 በአንዳንድ አካባቢ ከመደኛ በላይ መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር ስለሚችል የበልግ አብቃይ የሆኑ አካበቢዎች ውሃ በማሳ ላይ እንዳይተኛ የማንጠፍጠፍ ስራ እንዲሰሩ የብሔራዊ ሜትዮሮሎጂ ኤጀንሲ አሳሰበ።

በጥሩ ሁኔታ የገባው የዘንድሮ የበልግ ወቅት ወደመጨረሻው ላይ መዋዥቅ ቢከሰት እንኳን ተገቢውን ጥንቃቄ ለመውሰድ እንዲቻል የኤጀንሲውን መረጃዎች መከታታል እንደሚያስፈልግ አስገንዝቧል።

የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አህመዲን አብዱልከሪም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የበልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ያለው እርጥበትና የዝናብ ስርጭ ጥሩ ነው።

በመሆኑም የአገሪቱ የበልግ አብቃይ አካባቢዎች ላይ የእርሻ ሥራ፣ የማሳና የዘር ዝግጅት የሚካሄድበት ወቅት ነው።

በተለይም በመጋቢት ወር የዝናቡ ሁኔታ እየተጠናከረ ስለሚመጣ ለበልግ እርሻ ሥራዎች፣ ለአፈር እርጥበት መጠናከርና ዘር ለመዝራት እንዲሁም ለአርብቶ አደርና ለከፊል አርብቶ አደሮች አካባቢ ለመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ለግጦሽ ሳር አቅርቦት አወንታዊ ጎን ይኖርዋል።

ይሁንና በአንዳንድ የበልግ አብቃይ አካባቢዎች ላይ ከመጠን በላይ የዝናብ መጠን ሊኖር ስለሚችል ውሃ በማሳ ላይ እንዳይተኛ የማንጣፈፍ ስራዎችን  ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተለይም ደረቅ እርጥበት ሁኔታ በሚጠበቅባቸው ቦታዎች ላይ ከወዲው የዝናብ ውሃ ማቆር ሥራዎን ማከናወን እንደሚገባም አክለዋል።

የዘንድሮ የበልግ ዝናብ አጀማመርና አገባብ በሚፈለገው ሁኔታና ጥሩ ሲሆን በዝናብ ስርጭቱ እንደ አገር የሚያሰጋ ምንም ነገር የለም።

ነገር ግን የአገሪቷና አለም አቀፍ ተሞክሮ እንደሚያሳየው የበልግ ዝናብ የመለዋወጥና የመዋዠቅ ባህሪ እንዳለው ገልጸው ስለሆነም በቀጣይ የሚኖረውን ትንበያ በመከታተል ተገቢውን ክትትል ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ኤጀንሲው ከዚህ በፊት የሚሰጣቸው የትንበያ አገልግሎቶች 76 በመቶ የነበሩ ሲሆን ከጥቂት ዓመታት ጀምሮ በሰው ሃይል ብቃትና በቴክኖሎጂ ማሻሻል ላይ በሰሯቸው ስራዎች በአሁኑ ወቅት የሚሰጣቸው የትንበያ አገልግሎቶች ከ80 በመቶ በላይ መድረሱን አቶ አህመዲን አመልክተዋል።

በዚህም በየትኛውም የአገሪቷ አካበቢ የሚኖር ሰው የህብረተሰቡ የብሔራዊ ሜትዮሮሎጂ ኤጀንሲ ትንበያዎችን የመጠቀም አቅሙ ከፍ ያለ ሲሆን በቀጣይም አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።