መንግሥት በኢትዮጵያ የስቶክ ማርኬትን ለማስጀመር እንቅስቃሴ እያደርኩ ነው አለ

43

አዲስ አበባ የካቲት 29/2011 መንግስት የነጻ ገበያ ሥርዓት የሆነውን "የስቶክ ማርኬት" በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ።

መንግሥት በዚህ ዓመት መጀመሪያ የነጻ ኢኮኖሚ ሕግጋትን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስቀድሞ መጠቆሙ ይታወሳል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ፤ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የዲጂታል ገበያ ለመዘርጋት እየተሰራ ነው።

የዲጂታል ገበያ መንግሥት በቅርቡ ይፋ ባደረገው የመንግሥት ሥራ ዝርዝር (ዳሽ ቦርድ) ላይ ከአንኳር የምጣኔ ኃብት አቅጣጫ መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት "የካፒታል ገበያ" በአገሪቱ ለመዘርጋት የሚያስችል ፍኖተ-ካርታ በብሔራዊ ባንክ እየተዘጋጀ መሆኑን ነው ያስረዱት።

የስቶክ ማርኬት በጣም ውስብስብ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸው ምን አይነት የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች በጥልቀት እየተጠኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በተለይም የካፒታል ገበያ ደላሎች ወይንም የዘርፉ ባለሙያዎችን የመለየትና የማወቅም ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በስቶክ ማርኬት "ከየት እንጀምር? ለምሳሌ የመንግሥት ቦንዶችን ከመሸጥ እንጀምር ወይስ የተወሰኑ የግል ዘርፉን እናስገባ" የሚለውንም መንግስት እየተመለከተ ነው ብለዋል።

ይህም ደግሞ የስቶክ ማርኬት የመጀመሪያ ምዕራፍ በማጠናቀቅ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ የካፒታል የስቶክ ማርኬት ሙሉ በሙሉ ለመድረስ ያስችላል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም