በመዲናዋ የተፈጠረው የኤሌክትሪክ መቋረጥ ችግር እስከ ዛሬ ምሽት ይፈታል ተባለ

163

አዲስ አበባ የካቲት29/2011 በአዲስ አበባ ከተማ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው የኤሌክትሪክ መቋረጥ ዛሬ ምሽት እንደሚፈታ የመዲናዋ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ክፍሌ "ለኤሌክትሪክ መቋረጡ ዋና መንስኤው ምንድን ነው? ለሚለው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል።

ስራ አስኪያጁ በሰጡት ምላሽ ዋና መንስኤው በከተማዋ ያለው መስመር ያረጀ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ በመዝነቡ መስመሮቹ እርስ በርሳቸው በመነካካት፣ አንዳንዶቹም የመበጠስ አደጋ ስላጋጠማቸው ነው።

በአንዳንድ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ መስመሮች ላይ ዛፍ እንደወደቀባቸው የገለጹት አቶ በቀለ አሮጌውና አዲስ የተዘረጋው መስመር በነፋስ አማካይነት በመገናኘታቸው ጭምር ችግሩ እንደተፈጠረ አስረድተዋል።

በተለይም ቀድሞ የነበረው የኤሌክትሪክ መስመርና አዲስ የተዘረጋው የኮንክሪት መስመር ተጠጋግተው የተሰሩ በመሆኑ ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ ሲጥል ሁለቱ መስመሮች ተገናኝተው የኃይል መቋረጥ ችግር መፍጠሩን አብራርተዋል።

በቃለ መጠይቁ "ችግሩን ለመፍታት ምን እየሰራችሁ ነው? እስከ መቼስ ሊፈታ ይችላል? "ለሚለው ጥያቄ በአሁኑ ወቅት በቂ የሰው ኃይል በማሰማራት የጥገናና አሮጌውን መስመር የማንሳት ስራ እያከናወንን ነው ብለዋል።

"ኃይል ተቋርጦባቸው ጥገናቸው የተጠናቀቁ ቦታዎችም ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ እያደረግን ነው" ያሉት ስራ አስኪያጁ አብዛኛው ችግር ያጋጠማቸው አካባቢዎች እስከ ዛሬ ምሽት ድረስ ኤሌክትሪክ እንደሚያገኙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም