የአሶሳ ጉምሩክ ጣቢያን በአዲስ መልክ የማደራጀት ሥራ እየተሰራ ነው

73

አሶሳ የካቲት 28/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቆጣጠር የአሶሳ ጉምሩክ ጣቢያን በአዲስ መልክ የማደራጀት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተገለጸ፡፡

የኮንትሮባንድ ንግድ ላይ ከክልሉ ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአሶሳ  ከተማ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የጅማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ደረጄ ካሳሁን በክልሉ በኩል በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገቡ ሸቀጦች መካከል አልባሳት፣ መዋቢያ ዕቃዎች፣ የመግብ ዘይትና ስኳር እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ከሚወጡት መካከል የቁም እንስሳት፣ የዱር እንስሳት ውጤቶች፣ ቡናና የወርቅ ምርቶች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

አቶ ደረጄ እንዳሉት በጅማ ቅርንጫፍ የአሶሳ መቅረጫ ጣቢያ የሚይዛቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መጠን በ2006 ዓ.ም ከነበረበት 14 ሚሊዮን ብር በ2010 ወደ 20 ሚሊዮን ብር ከፍ ብሏል፡፡

"ይህም የፍተሻ ጣቢያው አቅም ማደግ ሳይሆን የህገ-ወጥ ነጋዴዎች አቅም እየተጠናከረ መምጣቱን ያሳያል" ብለዋል።

በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ አንዳንድ አመራሮች ከኮንትሮባንድ ንግድ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ መሆናቸው ለችግሩ መባባስ በምክንያትነት እንደሚጠቀስ ጠቁመዋል።

እንደአቶ ደረጄ ገለጻ እስከ 15 ዓመት በሚያስቀጣ የኮንትሮባንድ ንግድ ላይ የተሳተፉት ግለሰቦችን በስድስት ወራት ከመልቀቅ ጀምሮ ያለአግባብ የዋስትና መብት በመስጠት ወንጀለኞች እንዲሰወሩ የሚያደርጉ የፍትህ አካላት አሉ፡፡

በጉምሩክ ሰራተኞች በኩልም ቢሆን የስነ-ምግባርና የሙስና ችግሮች መኖራቸውን አቶ ደረጀ ገልጸዋል።

በአንጻሩ በክልሉ ጠረፍ አካባቢ የሚገኘው ማህበረሰብ እና በተለይ የቶንጎ ልዩ ወረዳ ሚኒሻ አባላት የኮንትሮባድ ንግድን ለመቆጣጠር እገዛ ማድረጋቸውን አቶ ደረጀ አስረድተዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል በኮሚሽኑ የአሶሳ ቅርንጫፍን በአዲስ መልክ በማዋቀርና ተጠሪነቱን በቀጥታ ለኮሚሽኑ ለማድረግ የሚያስችል አደረጃጀት እየተዘረጋ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በአዲስ መልክ የሚዋቀረው ቅርንጫፉ የክልሉን ህዝብና ከቀበሌ እስከ ክልል ያለውን አደረጃጀት እንደሚያማክል ጠቁመዋል፡፡

አሶሳ እና አካባቢውን ጨምሮ አልመሃል፣ ባምዛ፣ ጊዘን እና ኩርሙክ የተባሉ የጠረፍ ከተሞች ዋነኛ የትኩረት አካባቢዎች እንደሚሆኑም ተናግረዋል፡፡

ከውይይት ተሳታፊዎች መካከል በኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት የአሶሳ ብዝሃ ህይወት ማዕከል ባለሙያ ወይዘሪት ደጊቱ ደረሰው  ኢትዮጵያ ለህክምና የሚውሉ በርካታ እጽዋቶችን በህገ-ወጥ ንግድ እያጣች መሆኑን አስታውቀዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አስተባባሪ ሃጂ አብዱላሂ ኡመር በበኩላቸው የኮንትሮባንድ ንግድ በሃይማኖት ጭምር ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል።

ለአንድ ቀን በተካሄደው በዚህ የውይይት መድረክ ላይ 30 የሚጠጉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም