ለአምቦ ከተማ ልማትከ ህብረተሰቡና ድርጅቶች ከ63 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ

51

አምቦ  የካቲት 28/2011 የአምቦ ከተማን በጋራ እናልማ በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀ  የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከተለያዩ ድርጅቶችና  ህብረተሰብ ክፍሎች ከ63 ሚሊዮን በላይ ብር ድጋፍ ተገኘ፡፡

የአምቦ ከተማ የልማት ኮሚቴ አሰባሳቢና የከተማው አስተዳደር ከንቲባ  አቶ ተረፈ በዳዳ እንደገለጹት  ዛሬ በአምቦ ከተማ  በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም የተገኘው ገቢ ቀደም ሲል ቃል ከተገባው 450 ሚሊየን ብር ውስጥ ነው፡፡

ገንዘቡን በስጦታ ያበረከቱት ባለሃብቶች ፣ባንኮች  ፣ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ስምንት የከተማ አስተዳደሮችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡

በተጨማሪ የምዕራብ ሸዋ ዞንንና የአምቦ ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች የአንድ ወር ደመወዛቸውን  ለመስጠት ተስማምተዋል ፡፡

በሚሰበሰበው የገንዘብ ድጋፍ በአምቦ ለማከናወን ከታቀዱት ውስጥ አለም አቀፍ ስታዲዮም፣ የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን የአርት ጋለሪ፣ የከተማ  የውስጥ ለውስጥ  መንገድ ግንባታና ለወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር ፓርክ  ይገኙበታል፡፡

ባለፈው ሳምንት በሀያት ረጀንሲ ሆቴል በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም  ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለአምቦ ልማት እንዲውል ያበረከቱት ሰዓት ለጨረታ በማቅረብ አምስት ሚሊየን ብር መገኘቱንም አስታውሰዋል፡፡

ለልማቱ አንድ ሚሊዩን ብር የሰጡት  አቶ ሰይድ ዳምጠው በሰጡት አስተያየት  " የአምቦ ከተማ  የእድሜዋን ያህል ባለማደጓ ይቆጨኝ ነበር አሁን በዚህ ፕሮግራም ተሳትፌ ድጋፍ በመስጠቴ በጣም ደስ እያለኝ ለወደፊቱም እቀጥላለሁ "ብለዋል፡፡

ሁለት ሚሊዮን ብር የለገሱት አቶ ዮናስ ካሳሁን  በበኩላቸው በቀጣይም የዚህን ያህል ገንዘብ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል፡፡

የኦዲፒ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ታዬ ደንደአ በፕሮግራሙ ስነስርዓት ወቅት አምቦን ለማሳደግ  ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተባብረው በልማቱ ስራ በመሳተፍ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም