በህገወጥ መንገድ ሰዎችን አሳፍረው ከሀገር ለማስወጣት የሞከሩ ሁለት የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ተያዙ

87

ሰመራ የካቲት 28/2011 በህገ ወጥ መንገድ 75 ሰዎችን አሳፍረው  በጂቡቲ በኩል ወደአረብ ሀገር ለማስወጣት የሞከሩ ሁለት የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ዛሬ መያዙን የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በኮሚሽኑ የአቤቱታ ምርመራ ወሳኝ የስራ ሂደት ተወካይ ዋና ሳጂን ሳልህ ሲብሌሌ ለኢዜአ እንደገለጹት ከመቀሌ ተነስተው 75 ሰዎች በማሳፈር ድንበር ለማሻገር ሲሞክሩ የተያዙት  አውቶቡሶቹ  ታታ የተባሉ ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡

በአፋር ክልል ለጅቡቲ  ቅርብ በሆነው ኮሪ ወረዳ ልዩ ስሙ ስልሳ በሚባል አካባቢ በክልሉ ጸጥታ ኃይል ከተያዙ ተሽከርካሪዎች መካከል አንደኛው 30 ሰዎችን አሳፍሮ የነበረ የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 4-14746 ኢት የሆነ ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ቀሪዎቹን ሰዎች አስፍሮ የተገኘ የታርጋ ቁጥሩ  ኮድ 3-51186 ኢት  መሆኑን  ዋና ሳጂን ሳልህ አስረድተዋል፡፡

ከአውቶቡቹ ውስጥ ንብረትነቱ የመንግስት በሆነው የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 4-14746 ኢት ተሽከርካሪ ተሳፍረው ከነበሩት 30 ሰዎች እያንዳንዳቸው 700 መቶ ብር ለሾፌሩ  መክፈላቸውን  ለፖሊስ በሰጡት ቃል መግለጻቸውን  አውስተዋል፡፡

የሁለቱም አውቶቡሶች አሽከርካሪዎች ከነረዳቶቻቸው እንዲሁም  75ቱ ሰዎች ለፌዴራል ፖሊስ ሚሌ ዲቪዥን ተላልፈው መሰጠታቸውን ዋናሳጅን ሳልህ አስታውቀዋል፡፡

ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተነስተው በአፋር ክልሉ በኩል የሚደረጉ ህገ-ወጥ የሰዎችን ዝውውር ተለዋዋጭ ስልቶችን በመጠቀም እየጨመረ መጥቷል፡፡

በተያዘው ዓመት  በተደጋጋሚ በህገወጥ መንገድ ብዛት ያላቸው ሰዎችን ወደ አረብ ሀገር ለማሻገር ሲሞክሩ  መያዛቸውን ዋናሳጅን ሳልህ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም