ከአውሮፕላን ነዳጅ በስተቀር የሁሉም ነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ በመጋቢት ወርም ባለበት ይቀጥላል

58

አዲስ አበባ የካቲት 28/2011 በኢትዮጵያ ከአውሮፕላን ነዳጅ በስተቀር የሁሉም ነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ በመጋቢት ወርም ባለበት እንደሚቀጥል የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመስከረም 2001 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባው የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ በየወሩ እንዲከለስ መመሪያ ማስቀመጡ ይታወሳል።

ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በመጋቢት ወር ከአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ በስተቀር የሌሎች ነዳጅ ምርቶች ዋጋ ባለበት የሚቀጥል ይሆናል።

የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ከአንድ ዓመት በላይ ለውጥ ሳይደረግ በመቆየቱና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች በሁሉም የነዳጅ ምርቶች ላይ በህዳርና በየካቲት ወር 2011 ዓ.ም መጠነኛ ማስተካከያ ማድረጉን ሚኒስቴሩ አስታወሷል።

ነገር ግን በመጋቢት ወር ላይ መንግስት የኢትዮጵያ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል ለማስቻል በየካቲት ወር ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ ከየካቲት 27 ጀምሮ እስከ መጋቢት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ከአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ በስተቀር ባለበት እንዲቀጥል ወሰኗል።  

የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ አንድ ሊትር በየካቲት ወር ይሸጥበት ከነበረው 20 ብር ከ 62 ሳንቲም በዓለም ወቅታዊ ዋጋ አማካይነት ተሰልቶ በተገኘው ልዩነት 2 ብር ከ12 ሳንቲም በመጨመር በሊትር ብር 22 ከ74 ሳንቲም እንዲሆን ተደርጓል።

በዓለም ገበያ የሚኖረውን የነዳጅ ዋጋ መነሻ በማድረግ እንደ አስፈላጊነቱ የዋጋ ማስተካከያዎች ሊደረጉ እንደሚችሉ ሚኒስቴሩ አክሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም