በአራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ የመረጃ መረብ ጥቃት እንዳይፈፀም በቂ ዝግጅት ተደርጓል-ኤጀንሲው

714

የካቲት 28/2011 በኢትዮጵያ ለአራተኛ ጊዜ ለሚካሄደው የሀገር አቀፍ የህዝብና ቤት ቆጠራ የመረጃ መረብ ጥቃት እንዳያጋጥም ለመከላከል በቂ ዝግጅት መደረጉን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ገልጿል።

በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳፊ ገመዲ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ለአራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ በቂ የሰው ሃይል እና ቴክኖሎጂ መመደቡን ተናግረዋል።

መንግሥት የዘንድሮውን የህዝብና ቤት ቆጠራ ከሰው ንከኪ ነጻ በሆነ መንገድ ለማካሄድ ቁርጠኛ በመሆኑ ከቆጠራ ካርታ ጀምሮ ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ነው የተናገሩት።

በቆጠራ ሂደቱ መሰናክሎች እንዳያጋጥሙ፣ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ያነሱት አቶ ሳፊ የመረጃ መረብ ጥቃትን ለመከላከልም ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በቆጠራ ሂደቱ የመረጃ መረብ ጥቃትን ለመከላከል ከአንድ ዓመት ተኩል ጀምሮ ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጄንሲ ጋር እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ቆጣሪዎች መረጃቸውን ለተቆጣጣሪያቸው በብሉቱዝ ይልካሉ፤ ተቆጣጣሪው ለአስተባባሪው በብሉቱዝ ይልካል ብለዋል።

የኔትወርክና የመብራት መቆራረጥ እንዳይኖር ከቴሌ፣ መብራት ሃይል፣ ከኢንሳ፣ ከመገናኛና ኢንፎርሜሽን፣ ከሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።

የመብራት መቆራረጥ ቢያጋጥም እንኳ 126 ሺህ ተጠባባቂ የሃይል ቋቶች መገዛታቸውን ነው የነገሩን።

አስተባባሪው ለህዝብና ቤት ቆጠራ መረጃ ማስተላለፊያ በተዘጋጀውና ከሰርቨር ውጪ በሆነው በቨርቹዋል ፕራይቬት ኔትወርክ አማካይነት ወደ ማዕከል የመረጃ ቋት ይልካል ነው ያሉት።

የህዝብና የቤት ቆጠራ መረጃ ልውውጡ ከየትኛውም የሰርቨር መስመር ንክኪ እንዳይኖረው ለማድረግ ኢትዮ ቴሌኮም 37 ሺህ ካርዶችን መስጠቱን ገልጸዋል።

ለቆጠራው ዓላማ ብቻ የሚውሉ ታብሌቶች በዓለም አቀፋዊ ጨረታ ተገዝተው በሶስት ጊዜ ሙከራ አስተማማኝነታቸው መረጋገጡን አቶ ሳፊ ገልጸዋል።

የተገዙት ቴኬኖሎጂዎች በተለያየ የአየር ጸባይና መልክዓ ምድራዊ ሁኔታ ተሞክረው ዝግጁ መሆናቸውን ነው ያነሱት።

በቆጠራው 152 ሺህ ቆጣሪዎችና 37 ሺህ ተቆጣጣሪዎች እንደሚሳተፉና ስልጠና ተሰጥቷቸው የተግባር ፈተና ከወሰዱ በኋላ ወደ ቆጠራው እንደሚገቡ ገልጸዋል።

ቆጣሪዎችን የሚያሰለጥኑ 8 ሺህ ባለሙያዎች በመላ ሀገሪቱ ስልጠና እየተሰጣቸው ሲሆን የቆጣሪዎች ስልጠና መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም ይጀመራል ብለዋል።

ቴክኖሎጂው ቆጣሪዎች የሚመቻቸው ቦታ ላይ ብቻ ሆነው ቆጠራ እንዳያካሂዱ በጂፒኤስ የት ላይ እንደደረሱ መከታተል ስለሚቻል ማጭበርበር አይቻልም ብለዋል፤

ታብሌቱን ለግላዊ መረጃ ለመቀጠም የሚፈልጉ ቢኖሩ አይሰራም፤ ምክንያቱም ቴክኖሎጂው ለህዝብና ቤት ቆጠራው ዓላማ ብቻ የተሰራ መሆኑን ነው ያነሱት።

በኤጀንሲው የስነህዝብ ዳይሬክቶሬት የስታትስቲክስ ባለሙያ አቶ ተከተለው በሃይሉ እያንዳንዱ ታብሌት በመለያ ቁጥር በዋና የመረጃ ቋት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።

በታብሌቱ ላይ የቆጠራ ካርታ፣ የካርታ መግለጫ፣ ቦታ ጠቋሚ እና የመጠይቅ ቅፆች እየተጫኑ እየታሸጉ ነው፤ በቀጣይ ወደየቆጠራ አካባቢዎች ይጓጓዛሉ ብለዋል።