በሶማሌ ክልል ሁለተኛው የኩፍኝ በሽታ ክትባት መሰጠት ተጀመረ

639

ጅግጅጋ የካቲት 28/2011 በሶማሌ ክልል ሁለተኛው የኩፍኝ በሽታ ክትባት እየተሰጠ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።  

በክልሉ ጤና ቢሮ የእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎት አጠባበቅ ቡድን መሪ አቶ አብዲሸኩር አብዲላሂ ለኢዜአ እንደገለጹት ክትባቱ ከትናንት ጀምሮ እየተሰጠ ያለው በክልሉ በሚገኙ 942 የጤና ተቋማት ነው።

ጤና ተቋማቱ ቀደም ሲል ለህፃናት የኩፍኝ መከላከያ ክትባት በመደበኛው አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ናቸው።

አዲሱ የክትባት መርሃ ግብር ህጻናት በተወለዱ በዘጠኝ ወር ከሚሰጠው ክትባት የተለየና በ15ኛ ወራቸው ላይ የሚሰጥ መሆኑን ቡድን መሪው ተናግረዋል።

በቀጣይም በጤና ተቋማቱ በመደበኛነት ተጠናክሮ የሚሰጥ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ አቶ አብዲሸኩር ገለጻ በክልሉ ከሚገኙ 1 ሺህ 500 የጤና ተቋማት ውስጥ 942 ያህሉ ለክትባቱ አገልግሎት የሚውሉ ግብዓቶች ተሟልተውላቸው ክትባቱን መስጠት ጀምረዋል።

ሁለተኛው ክትባት በመጀመሪያው ዙር ክትባት 85 በመቶ የደረሰውን የህጻናት በሽታ የመከላከል አቅም ወደ መቶ ፐርሰንት የሚያሳድግ መሆኑ ተመልክቷል።

በጅግጅጋ ከተማ ካራ ማራ ሆስፒታል ልጃጀውን ሲያስከትቡ የነበሩት ወይዘሮ ሙሚና ድንቢል ኩፍኝ በአካባቢያቸው ለህፃናት ሕመም፣ አካል ጉዳትና ሞት ምክንያት መሆኑን ገልጸው ልጃቸውን ከእዚህ ለመታደግ ለማስከተብ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

የኩፍኝ በሽታ የኩፍኝ ቫይረስ በሚባል ረቂቅ ታህዋስያን የሚከሰትና በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው የሚዛመት በሽታው ነው።

ከፍተኛ ትኩሳት፣ ከፀጉር ጀምሮ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች የሚዛመት ጥቃቅን ሽፍታ፣ የዓይን መደፍረስ ወይም መቅላት፣ ከአፍንጫ የሚወጣ ፈሳሽ መብዛት ከበሽታው ምልክቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።