በባህር ዳር ከተማ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶችንና የሕክምና መሳሪያዎችን የሚያቃጥለው መሳሪያ ሥራ ሊጀምር ነው

49

ባህርዳር የካቲት 28/2011 በባህር ዳር ከተማ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶችንና የሕክምና መሳሪያዎችን ለማቃጠል የተከላ ሥራው እየተጠናቀቀ ያለው ዘመናዊ መሳሪያ ከአንድ ወር በኋላ ሥራ እንደሚጀምር ተገለጸ።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ድርጅት ባህር ዳር ቅርንጫፍ እንዳስታወቀው በቴክኖሎጂ የታገዘው ዘመናዊ መሳሪያ ተከላ ሥራ ከአንድ ወር በኋላ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል። 

የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ  አቶ አብዲሳ መንገሻ ለኢዜአ እንደገለጹት መሳሪያው በሰዓት 500 ኪሎ ግራም ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶችንና የሕክምና መሳሪያዎችን የማቃጠል አቅም አለው። 

በመድኃኒትቅመማ ክህሎት እጥረት እና  በአያያዝ ችግር ምክንያት መድኃኒቶች የመገልገያ ጊዜ አልፎባቸው ለብልሽት እንደሚዳረጉ አመልክተዋል።

እስካሁን ድረስ የአግልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው  መድኃኒቶችና የሕክምና መሳሪያዎች በተበላሹበት የጤና ተቋም አካባቢ በግላጭ ቦታ እየተቃጠሉ ሲወገዱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

መድኃኒቶች ኬሚካል ይዘት ስላላቸው በባህላዊ መንገድ ሲቃጠሉ የሚወጣው ጭስ በሰዎች፣ በእንስሳትና በእጽዋት ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ አመልክተዋል።

ጭሱ ሰዎችን ለሳምባ በሽታ፣ ለመተንፈሻ አካላትና ለተለያየቱ የዓይንና የጆሮ በሽታዎች እንደሚዳርግም አቶ አብዲሳ አመልክተዋል።

"ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትም የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ድርጅት ከግሎባል ፈንድ በተገኘ የሁለት ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ዘመናዊ የመድኃኒት ማቃጠያ መሳሪያ ተከላ ሥራ እየተጠናቀቀ ነው" ብለዋል።

የተከላ ስራው ባለፈው ሐምሌ ወር የተጀመረው የባህር ዳር ቅርንጫፍ ዘመናዊ የመድኃኒት ማቃጠያ መሳሪያ በአሁኑ ወቅት ሥራው ከ80 በመቶ በላይ ተጠናቋል።

በቀጣይ ሚያዚያ ወር 2011 ዓ.ም የተከላ ሥራው ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ቀደም ሲል ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶችና የሕክምና መሳሪያዎች ዘመናዊ ባልሆነ መንገድ ሲያውሰግዱ እንደነበረና ይህም ለበሽታ ሲያጋልጣቸው እንደነበረም አቶ አብዲሳ ተናግረዋል።

አቶ አብዲሳ እንዳሉት ቴክኖሎጂው መድኃኒቶችንና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎችን አንድ ሺህ 200 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሚደርስ ከፍተኛየሙቀት መጠን ጭስ አልባ በሆነ መልኩ በማቃጠል ወደ አመድነት መቀየር የሚያስችል ነው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በየጤና ተቋሟቱ እስከ ሁለት በመቶ የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች መኖር   የሚጠበቅ ነው።

በባህር ዳር ቅርንጫፍ በዓመት ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግባቸው መድኃኒቶች የሚገዙ ሲሆን የብክነት መጠኑ  ከ1  ነጥብ 4 በመቶ በታች መሆኑ ታውቋል።

የዘመናዊ መሳሪያ ተከላ ሥራ ተጠናቆ ወደ ስራ ከገባው የአዳማ ቅርንጫፍን በተጨማሪ በባህር ዳር፣ መቀሌ፣ ደሴ፣ ጅግጅጋ፣ ሀዋሳ፣ ጅማ፣ ነቀምትና ድሬዳዋ የተከላ ስራው በመከናወን ላይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም