በጎርፍ አደጋ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አራት ሰዎች ሕይወት አለፈ

73

ደብረ ብርሃን የካቲት28/2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንኮበር ወረዳ በጣለው ከባድ ዝናብ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አራት ሰዎች በጎርፍ ተወስደው ሕይወታቸው ማለፉን የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡   

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ዋና ኢኒስፔክተር ይመኑ መንገሻ ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው በወረዳው ደረፎ ቀበሌ ልዩ ስሙ "ንፋሶ ጎጥ" ተብሎ በሚጠራው አካባቢ  የካቲት 26 ቀን 2011 ዓ.ም በጣለ ከባድ ዝናብ ነው፡፡

የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ ጨው በሌ ተብሎ የሚጠራው ወንዝ ድንገት በጎርፍ በመሙላቱ አደጋው መድረሱን ተናግረዋል፡፡

በደራሽ ጎርፍ አደጋው እህል ለማስፈጨት ወደሌላ አካባቢ ሄደው ወደቤታቸው በመመለስ የነበሩ አራት የአንድ ቤተሰብ አባላት ሕይወታቸው አልፏል።

ዋና ኢኒስፔክተር ይመኑ እንዳሉት በአደጋው ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 28 ዓመት የሚገኙ የቤተሰብ አባላት ናቸው፡፡

የሟቾቹ አስክሬ የአካባቢው ህብረተሰቡ ለብዙ ሰዓታት ፍለጋ ካደረገ በኋላ መገኘቱን የገለጹት ዋና ኢኒስፔክተር ይመኑ ፣ የቀብር ስንስርአታቸውም ትናንት ዘመድ ወዳጆቻቸው በተገኙበት በአካባቢው በሚገኝ አቦ ቤተክርስቲያን መፈፀሙን አስታውቀዋል፡፡

ህብረተሰቡ የበጋ ዝናብን እንደቀላል መመልከት እንደለሌበትም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም