ከቦታ እደላ ጋር ተያይዞ ወንጀል በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ አስታወቀ

59

መቀሌ የካቲት 27/2011 በትግራይ ክልል ከመኖሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ እደላ ጋር ተያይዞ ወንጀል በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮ ኃላፊው አቶ አማኑኤል አሰፋ ከንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ጋር በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት በከተሞች ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው።

የክልሉ መንግስት ችግሩን ለማቃለል ካለፈው ዓመት ጀምሮ የመኖሪያ ቤት የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር አውጥቶ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

መንግስት ያወጣውን አሰራርና መመሪያ በተገቢው መንገድ ከመጠቀም ይልቅ መመሪያውን በማዛባት የተለያዩ ወንጀሎች እየተፈፀሙ መሆናቸው ተናግረዋል።

ከቀበሌ መታወቂያ ካርድ አወጣጥ ጀምሮ የመኖሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ ለማግኘት ሲባል ጋብቻን የሚያክል ፍቺ እስከመፈፀምና የነበረን መኖሪያ ቤት ለሌላ ሰው አሳልፎ የመስጠት ሁኔታ እየተስተዋሉ መሆናቸውን አቶ አማኑኤል አስታውቀዋል።

"የክልሉ ፍትህ ቢሮ ከክልሉ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ከመኖሪያ ቤት ማስገንቢያ ቦታ ዕደላ ጋር በተያያዘ  በሁሉም የክልሉ ከተሞች ሰነዶችን የማጣራት ስራ በቅርቡ ያካሂዳል" ብለዋል።

የክልሉ መንግስት የሚያካሂደውን የማጣራት ሥራ ተከትሎ ህጋዊ እርምጃ ከመውሰድ ወደ ኃላ እንደማይልም አቶ አማኑኤል አስጠንቅቀዋል።

የክልሉ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አታክልቲ ገብረሕይወት በበኩላቸው፣ በክልሉ የተጀመረው የመኖሪያ ቤት ግንባታ ቦታ እደላ በክልሉ ባሉ 12 ከተሞችም በቀጣይነት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረው መመሪያ እንዲሻሻል መደረጉን ገልጸው፣ በተስተካከለው አዲሱ መመሪያ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ሰዎች ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ማስረጃ በማጣራት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንዲያገኙ የሚደረግ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም ቦታ ከተሰጣቸው ማህበራት ጋር ግንባታ ለማካሄድ ውል አስረው ሥራ የጀመሩና በተለያዩ መንገዶች በውላቸው መስራት ያልተገኙ ኮንትራክተሮችን ማህበራቱ ህጋዊ ሰውነት ያላቸው በመሆኑ ተከታትለው እንዲያስፈጽሙ አሳስበዋል።

የክልሉ መንግስት በቀጣይም መሰል ችግር እንዳያጋጥም ተገቢውን ክትትልና ጥንቃቄ የሚያደርግ መሆኑን አቶ አታክልቲ ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም