ክልል አቀፍ የደኢህዴን አመራሮች መድረክ ነገ በሀዋሳ ይጀመራል

47

ሀዋሳ የካቲት 27/2011 የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/ ክልል አቀፍ የአመራሮች መድረክ ነገ በሀዋሳ ከተማ እንደሚጀምር የድርጅቱ  ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነትና ሚዲያ መምሪያ ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ሜጎ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ መድረኩ የደኢህዴን ስራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሜቴ በቅርቡ ባሰቀመጠው ውሳኔ ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡

ስራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሜቴ ከየካቲት 12 እሰከ 18/2011ዓ.ም በአርባምንጭ ከተማ ውይይት ማድረጉን አስታውሰዋል።

በዚህም በሀገራዊና  ክልላዊና ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች  እንዲሁም የልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮችን በዝርዝር መገምገሙን ተናግረዋል።

ነገ በሀዋሳ የመጀመረው መድረክም ክልላዊ የአመራር መድረኩ የተቀመጠውን አቅጣጫ መሰረት አድርጎ እንደሚወያይ አስረድተዋል፡፡ 

አመራሩ በአካባቢው ባሉ መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎችና ክልላዊ ሁኔታዎች ላይም በጥልቀት እንደሚመክር ይጠበቃል፡፡

" በሂደቱም የአመለካከትና የተግባር አንድነት በማምጣት ከሀገራዊ ለውጡ ህዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ይመከራል " ሲሉ  አቶ ገዛኸኝ አመልክተዋል፡፡ 

መድረኩ ለአራት ቀናት እንደሚቆይና  ከ2 ሺህ በላይ በወረዳ ፣በዞኑንና በክልል ደረጃ የሚገኙ  አመራሮች እንደሚሳተፉ  አመልክተው ተመሳሳይ መድረክ እስከ ቀበሌ ድረስ እንቀሚቀጥል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም