በወልድያ ከተማ በ84 ሚሊዮን ብር ወጪ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው

56

ወልዲያ  የካቲት 27/2011 በወልድያ ከተማ የሚስተዋለውን የመሰረተ ልማት አቅርቦት እጥረት ለመፍታት በ84 ሚሊዮን ብር ወጪ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የከተማው አገልግሎት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ የቤቶችና መሰረተ ልማት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ጎሽየ አምባው እንደገለጹት ከተማዋ በተራራ የተከበበች በመሆኗ በተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ ይከሰትባታል፡፡

ጎርፍን ለመከላከል በየዓመቱ ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ የጎርፍ መከላከያ ሥራ ሲከናወን መቆየቱንና በእዚህም ችግሩ ከጊዜ ወደጊዜ እየተቃለለ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

"ዘንድሮም የከተማዋን መሰረተ ልማት ለማጠናከርና በክረምት ሊከሰት የሚችለውን ጎርፍ ለመከላከል የሚያግዝ የልማት ሥራ በ80 ሚሊዮን ብር እየተሰራ ይገኛል" ብለዋል፡፡

እየተሰሩ ካሉት የመሰረተ ልማት ሥራዎች መካከልም የተፋሰስ ሥራ፣ በሽቦ አጥር የመሬት ድጋፍ ግንብ፣ የጌጠኛ መንገድ ንጣፍና የመሳሰሉት ሥራዎች ይጠቀሳሉ፡፡

የወልድያ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ በወልድያ ከተማ በክረምት ወቅት የሚከሰተውን ጎርፍ ለመቀነስ የሚያግዝ ግንብ በ4 ሚሊዮን ብር ወጪ እያሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የተቋማዊ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳዊት መለሰ እንዳሉት ወደ ከተማዋ የሚመጣውን ጎርፍ ለመቀነስ የሚያስችል የግንብ ስራ እየተሰራ ያለው በከተማዋ መልካቆሌ በተባለው ስፍራ ሸሌ ወንዝ ግራና ቀኝ ላይ ነው፡፡

በግንባታ ስራው በወንዙ የቀኝ ክፍል 120 ሜትር ርዝመትና አራት ሜትር ከፍታ ያለው ግንባታ ተካሄዶ ሰሞኑን መጠናቀቁን አስታውቀዋል።፡

በወንዙ የግራ ክፍልም ተመሳሳይ የግንባታ ሥራ መጀመሩን ጠቁመው "የግንባታ ሥራው እስከ መጪው ወር መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል" ብለዋል፡፡

የወልድያ ከተማ ከንቲባ አቶ መሀመድ ያሲን በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የከተማዋን የጎርፍ ስጋት ለመቀነስ የተቀናጀ ሥራ ሲሰራ መቆየቱንና አሁንም እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወልዲያ ከተማ በተራራ የተከበበች በመሆኗ በክረምት ወቅት ከተራራው አካባቢ ተጠራቅሞ በሚመጣ ጎርፍ በነዋሪው ላይ ችግር እያስከተለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታትም የተፋሰስ ልማትና አጋዥ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የወልድያ ከተማ ነዋሪ አቶ ባየው ዓለሙ በበኩላቸው በሚያዝያ 2008 ዓ.ም በጣለ ከባድ ዝናብ አካባቢው በጎርፍ ተጥለቅልቆ በርካታ ንብረት መውደሙን አስታውሰዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በተከታታይ በሰራቸው የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የጎርፍ መጥለቅለቅና በዚያ ምክንያትም ሲደርስ የነበረው ችግር እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም