የፕሪሚየር ሊጉ የአንደኛ ዙር ውድድር ክንውን ግምገማ ተካሄደ

51

አዲስ አበባ የካቲት 27/2011 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአንደኛ ዙር በስፖርታዊ ጨዋነት በተሰሩ ስራዎች መልካም ተሞክሮች መገኘታቸውን ክለቦች ገለጹ።

የፕሪሚየር ሊጉ የአንደኛ ዙር ውድድር ግምገማ ዛሬ ተካሄዷል።

የመቐለ ሰብዓ እንደርታ እግር ኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ ሽፈራው ተክለሃይማኖት እንደገለጹት አዲሱ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራር ከአንድ ዓመት በላይ በሜዳቸው ተጫውተው የማያውቁትን የትግራይና የአማራ ክልል ክለቦች በሜዳቸው እንዲጫወቱ ያደረገው ጥረት ሊመሰገን ይገባል።

እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ከሁለቱ ክልል (የአማራና ትግራይ) ክለቦች አመራሮችና ደጋፊዎች እንዲሁም ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርጎ ጉዳዩ እልባት እንደያገኝ ማደረጉ መልካም የሚባል ስራ ነው ብለዋል።

የክልሎቹ ክለቦች ያደረጓቸው ጨዋታዎች በሰላም መጠናቀቃቸውንና ይህም በመጀመሪያ ዙር በስፖርታዊ ጨዋነት ከተሰሩ ስራዎች እንደ መልካም ተሞክሮ ሊወሰድ ይገባዋል ብለዋል።

የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች ሲከሰቱ በደጋፊዎች መካከል ተነጋግሮ መፍትሄ ለመስጠት የሚደረገው ጥረትና በክለቦችና በፌዴሬሽኑ መካከል ችግሩን ለመፍታት ያለው ትብብርም በጠንካራ ጎን እንደሚታይ ጠቅሰዋል።

አሁንም በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚታዩ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶችን በጋራ በመፍታት ሁለተኛው ዙር በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።

የሲዳማ ቡና ዋና አሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉ የዘንድሮው ዓመት ውድድር ከመጀመሩ በፊት በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ውይይቶች መካሄዳቸውና ክለቦች ደጋፊዎቻቸውን በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ስልጠና መስጠታቸው ጥሩ የሚባል ጅምር እንደሆነ አንስተዋል።

ክለባቸው በመጀመሪያው ዙር ከወላይታ ዲቻ ጋር ጨዋታውን ሶዶ ላይ ማድረግ የነበረበት ቢሆንም በደቡብ ክልል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ አዲስ አበባ ስታዲየም መደረጉን አውስተዋል።

በሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች መካከል ጨዋታው ምንም አይነት ችግር እንደሌለና ችግሩ ያለው የክለቦቹ አመራሮች ጨዋታውን የማካሄድ ቁርጠኝነት በሚፈለገው ደረጃ አለመሆንና ጉዳዩ ፖለቲካዊ ይዘት መያዙ እንደሆነም አመልከተዋል።

እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ይህንኑ ጉዳይ ከግምት ውስጥ በማስገባት ክለቦቹ ቀጣይ ጨዋታቸውን በሜዳቸው እንዲያደርጉ አስፈላጊውን ጥረት እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

በሁለተኛው ዙር ዋንጫ ለማንሳትና ላለመውረድ የሚደረግ ጠንካራ ፉክክር ስለሚኖር ይህኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዳኞች አመዳደብና በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋልም ነው ያሉት። 

የሀዋሳ ከተማ እግር ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ ጣሃ አህመድ በበኩላቸው ዳኞች የሚሰሯቸው አንዳንድ ስህተቶች ቡድኖች ውጤት እንዲያጡ እያደረገ በመሆኑ የዳኞችን አቅም ከማጎልበት አንጻር በቂ ስራ እንዳልሰራ አመልክተዋል።

ዳኞች አንድ ቡድንን በተደጋሚ የማጫወት ሁኔታ በውድድር ዓመቱ የታየ ችግር እንደሆነና የዳኞች አመዳደብ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአንዳንድ የጨዋታ ኮሚሽነሮች ሪፖርትም ችግር አለበት ያሉት አቶ ጣሃ በሜዳ ላይ የተከሰተን ግልጽ ነገር የማድበስበስ ሁኔታ ይስተዋላል ብለዋል።

የመርሃ ግብሮች መቆራረጥ በአንደኛው ዙር ከታዩ ችግሮች መካከል መሆኑን ጠቅሰው በሁለተኛው ዙር በወጣላቸው መርሃ ግብር መሰረት እንዲካሄዱ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት 

የጸጥታ አካላት በደጋፊዎች ላይ ከልክ በላይ የሆነ ሃይል መጠቀምና የስታዲየም ጸጥታ እንዴት መከበር አለበት በሚለው ዙሪያ ክፍተት እንዳለባቸው ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እንዳሉት አዲሱ አመራር ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ የስፖርታዊ ጨዋነትን ጉዳይ መስመር ለማስያዝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል።

የአማራና የትግራይ ክልል ክለቦች በሜዳቸው እንዲጫወቱ የማደርግ ስራም በስኬት ተከናውኗል ብለዋል።

በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ከባለፈው የውድድር ዓመት በአንፃሩ የተሻለ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ ለዚህም ክለቦች ያበረከቱትን አስተዋፆ አድንቀዋል።

የዳኞችን አቅም ለመገንባት የተለያዩ ስልጠናዎች እየተሰጡ በመሆኑ ያሉባቸውን ክፍተቶች እንዲሞሉ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በጨዋታ ላይ አልፎ አልፎ ስህተት በሚሰሩ ዳኞችና ኮሚሽነሮች ሲያጋጥሙ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ጠቅሰው ቀጣይም ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል።

የውድድር መርሃ ግብሮች በተመለከተም ፌዴሬሽኑ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮችን ባማከለ መልኩ እያወጣ ሲሆን በሁለተኛ ዙር ውድድሩ ወጥነት ባለው መንገድ እንዲካሄድ አስፈላጊው ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

በስታዲየም ያለውን የጸጥታ አከባበር የተሻለ ለማድረግም ለጸጥታ አካላት ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል። 

ፌዴሬሽኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ያሉበትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዲፈቱ የሚያስችሉ ጥናቶችን አድርጎ የማሻሻያ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑና ለእግር ኳስ ልማት እየተከናወነ ያለውን ተግባር ክለቦች እንዲያግዙ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በመጀመሪያ ዙር በተደረጉ 120 ጨዋታዎች 457 ቢጫ ካርዶችና 16 ቀይ ካርዶች ተመዘዋል።

የፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር መርሃ ግብር መጋቢት 8 ቀን 2011 ዓ.ም ተጀምሮ ሰኔ 9 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም