በመካከለኛውና ታችኛው አዋሽ ተፋሰስ ሁለት ግዙፍ ግድቦች ሊገነቡ ነው

186

አዳማ የካቲት 27/2011 በመካከለኛውና ታችኛው አዋሽ ተፋሰስ 11 ቢሊዮን ብር በሆነ ወጪ ሁለት ግዙፍ ግድቦችን ለመገንባት የሚያስችል ጥናት መጠናቀቁን የአዋሽ ተፋሰስ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ ።

ግድቦቹ በአዋሽ ተፋሰስ በክረምት ወራት የሚከሰተውን የጎርፍ ስጋትና በበጋ ወራት በተፋሰሱ አካባቢ  እያጋጠመ ያለው የውሃ እጥረት የሚያቃልሉ ናቸው።

የአዋሽ ተፋሰስ ልማት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ አበጀ መንገሻ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የአዋሽ ተፋሰስ በርካታ ገባር ወንዞችን የሚያስተናግድ በመሆኑ በክረምት ወቅት በአካባቢው ህዝብ ፣ እንሰሳትና  ልማቶች ላይ ጉዳት የሚያስከትል ጎርፍ ሲፈራረቅበት ቆይቷል፡፡

በአንድ በኩል ጎርፉን በዘላቂነት ለማስቀረት ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የጎርፍ ውሃውን በመያዝ በበጋ ወራት የሚያጋጥመውን የውሃ እጥረት የሚያቃልሉ ሁለት ግዙፍ ግድቦችን መገንባት በማስፈለጉ ጥናት ተካሄዶ ለውሳኔ ሰጪው አካል መቅረቡን ተናግረዋል።

በጥናቱ መሰረት ለግድቦቹ ግንባታ 11 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚጠይቅ ያስታወቁት ስራ አስኪያጁ  ግድቦቹ የሚጠፋ ህይወትና ንብረት ከማዳን ባሻገር የጎርፍ ተፈናቃዮችን ከቦታ ቦታ ለማጓጓዝ ፣ በመጠለያ ለማስፈር ፣ የእለት ደራሽ ቀለብ ለማቅረብና መልሶ ለማቋቋም የሚወጣውን ከፍተኛ የሀገር ሀብት እንደሚቆጥብ አስረድተዋል።

የሁለቱ ግድቦች ጥናት ከአራት ዓመት በፊት  ተጀምሮ ዘንድሮ እንደተጠናቀቀ  የገለጹት አቶ አበጀ  በላይኛው አዋሽም በሚቀጥለው ዓመት የሚጠናቀቅ  ተመሳሳይ ጥናት መጀመሩን ጠቁመዋል።

የተቀናጀ የተፋሰስ እንቅስቃሴና የወንዝ አመራር ዳይሬክተር  አቶ ወንድአፍራሽ ወንድማገኝ በበኩላቸው ሁለቱ ግድቦች የሚገነቡት በአዋሽ ሰባት ኪሎና በሎጊያ አካባቢዎች እንደሆነ ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት በአዋሽ ሰባት ኪሎ አካባቢ የሚገነባው ግድብ 501 ሚሊዮን ሜትር ኩዩብ ውሃ የመያዝ አቅም ይኖረዋል፤  ከአሚባራ አስከ አፍአምቦ ድረስ የሚገኙ ለጎርፍ ተጋላጭ ቦታዎችን ከስጋት ነፃ የሚያደርግ ነው።

የዓሳ እርባታ ስራ ለማከናወንና ለአካባቢው ወጣቶች የስራ  እድል በመፍጠር ጭምር  ፋይዳው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል ።

በታችኛው አዋሽ ሎጊያ አካባቢ የሚገነባው ሁለተኛው ግድብ ደግሞ 470 ሚሊዮን ሜትር ኩዩብ ውሃ የሚይዝና ለተንዳሆ ግድብ አጋዥ የልማት አቅም ሆኖ እንደሚያገለግል ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም